የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቦይንግ ትብብር የኢትዮጵያና የአሜሪካንን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ያጠናክራል – አምባሳደር ኧርቪን ሆሴ ማሲንጋ::

Spread the love

የኢትዮጵያ አየር መንገድና ቦይንግ የደረሱበት የትብብር ደረጃ የኢትዮጵያና የአሜሪካንን ምጣኔ ኃብታዊ ግንኙነት ለማጠናከር ትልት አስተዋጽኦ ያደርጋል ሲሉ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ሆሴ ማሲንጋ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በአፍሪካ በዓይነታቸው የመጀመሪያ የሆኑ 20 ቦይንግ 777 ኤክስ 9 የተሰኙ ግዙፍ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከቦይንግ ኩባንያ ጋር በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሥምምነት አድርጓል።

በመርኃ-ግብሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢና የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳን ጨምሮ የአየር መንገዱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ሆሴ ማሲንጋና የቦይንግ ኩባንያ ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ፤ ይህ አውሮፕላን በግዙፍነቱና በዓይነቱ በአፍሪካ የመጀመሪያው መሆኑን ገልፀዋል።

አየር መንገዱ ትዕዛዝ ከፈፀመባቸው 20 የቦይንግ 777 ኤክስ 9 አውሮፕላኖች ውስጥ ስምንቱን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር እስከ 2030 የሚረከብ መሆኑን ጠቁመዋል።

አውሮፕላኖቹ እያንዳንዱ 440 መንገደኞችን የመያዝ አቅም ያላቸውና የደንበኞችን ምቾት መጠበቅ የሚችሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም አየር መንገዱን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል ብለዋል።

የቦይንግ ኩባንያ ከፍተኛ የንግድና ማርኬቲንግ ምክትል ፕሬዝዳንት ብራድ ማክሙለር በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ላይ ለቦይንግ ኩባንያ ስትራቴጂክ አጋር መሆኑን ገልፀዋል።

በቀጣይም አየር መንገዱ ያለው ሰፊ ፍላጎት ላይ በመመርኮዝ በጋራ ለመሥራት ዕቅድ ይዘናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ሆሴ ማሲንጋ በበኩላቸው፤ የቦይንግ ኩባንያና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያደረጉት የአውሮፕላን ግዥ ሥምምነት ሁለቱ ተቋማት የነበራቸውን ጠንካራ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑን ገልፀዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን የሁለቱን አገራት ኢኮኖሚ ለማሳደግም የላቀ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሳለፍነው ኅዳር ወር 2016 ዓ.ም በቅርቡ ከቦይንግና ከኤር ባስ የአውሮፕላን ኩባንያዎች በድምሩ 84 የመንገደኞች አውሮፕላኖችን ለመግዛት ሥምምነት ማድረጉ ይታወሳል።

በተመሳሳይ ሌሎች የአውሮፕላን ትዕዛዞችን ለማድረግ መታቀዱንም እንዲሁ።

አየር መንገዱ በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊየን ዶላር ከፍ ለማድረግና በዓመት 67 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ ነው ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *