የተጀማመሩ የልማትና የሠላም ግንባታ ተግባራት ከግብ እንዲደርስ ህዝቡ በጽናት ከመንግሥት ጎን መቆም አለበት – ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

Spread the love

ሀገራዊ ለውጡ እውን የሆነበትን 8ኛ ዓመትና የመጋቢት 24 ትሩፋቶችን የሚዘክር ታላቅ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በቦንጋ ከተማ ላይ ተካሄደ።

በድጋፍ ስልፉ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፥ ሀገራዊ ለውጡ በዘርፈ ብዙ ድሎች የታጀበ መኾኑን ተናግረዋል።

መጋቢት 24 አካታችና ኅብረ-ብሄራዊ የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ መሠረት የተጣለበት፣ ሀገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው የህግ ማሻሻያዎች የተደረገበት እንደኾነም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

በለውጡ መንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መመዝበገባቸውንና የዘመናት የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘታቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መመሥረትም የለውጡ አንዱ ትሩፋት ነው ብለዋል።

የተጀማመሩ የልማትና የሠላም ግንባታ ተግባራት ከግብ እንዲደርስ ህዝቡ በጽናት ከመንግሥት ጎን መቆም እንዳለበት ያስገነዘቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ መንግሥት ምላሽ ያላገኙ የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ቁርጠኛ እንደኾነ ተናግረዋል።

የህዝቦች አንድነት የሚፈታተኑ የውጥ ባንዳዎችን በጽናት በመታገል የአፍራሽ ሀይሎችን ተልዕኮ በማክሸፍ ቀጣይ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲኾን ህዝቡ የድርሻውን እንዲወጣም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተገኙ የልማት ድሎች ተጠናክረው እንዲቀጥል የዞኑ ህዝብ ያሳየው ድጋፍ የሚደነቅ መኾኑን ነው የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ የገለጹት።

የለውጡ መንግሥት በሁሉም ዘርፍ አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገቡ የዜጎችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መኾኑን የገለጹት አስተዳዳሪ፣ ህዝቡ በጽናት ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል።

የቦንጋ ከተማ ከንቲባ ተክሌአብ ቡሎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የከተማው ነዋሪዎችን የለውጡ መንግሥትን በመደገፍ በጽናት የቆመ መኾኑን ተናግረዋል።

አቶ እንዳሻው የዞኑ ኅብረተሰብ በነቂስ በመውጣት ላሳየው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በህዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች እና የኅብረተሰብ ክፍሎች በነቂስ በመውጣት ተሳትፈዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *