የልማት ተደራሽነትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት በለውጡ የተመዘገበ ትልቅ ድል ነው፦አቶ ፍቅሬ አማን

Spread the love

የመጋቢት 24 ታሪካዊ ቀን በሚዛን አማን ከተማ በድምቀትና በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጺያ ህዝቦች ከልልመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን በድጋፍ ሰልፉ ላይ ለውጡ ያመጣቸው ዋና ዋና ድሎች መካከል የልማት ተደራሽነትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት መሆኑን ጠቅሰው የህዝብ የራስን ራስ አስተዳደር ጥያቄ በተግባር መረጋገጡን ገልጸዋል።

በክልሉ የተጀመረው የኮሪደር ልማትና የአንድ መሶብ አገልግሎቶች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንደሚጠናከሩ ሲገልጹ በገጠር የሚካሄዱ የሽግግር ስራዎችን በማጠናከር የከተማና የገጠር ትስስርን ማሳለጥና የሌማት ትሩፋትን በማሳደግ በቤተሰብ ደረጃ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

እንዲሁም 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በክልሉ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ መንግስት የእዳ ክፍያን ብቻ ሳይሆን የእዳ መመለስ ስትራቴጂ እየፈጸመ መሆኑን እና የቀይ ባህር ጉዳይን በህጋዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች እንዳሉ ገልጸዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በንግግራቸው መጋቢት 24 በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የለውጥ መነሻና የዴሞክራሲ መንገድ መክፈቻ መሆኑን ገልጸው ብልጽግና ፓርቲ በሪፎርም መንገድ ተግዳሮቶችን ወደ ዕድል በመቀየር በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በዲፕሎማሲ ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገቡን አስታውቀዋል።

በዞኑ የከተማ ልማት፣ መሠረተ ልማት፣ ግብርናና ጤና ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችም ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በዚሁ የድጋፍ ሰልፍ የክልሉ ምክርቤት ዋና አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ፣ የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማንን ጨምሮ የክልል፣ የዞን እና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

በዓሉ በየአይነቱ ባህላዊ ትዕይንቶች፣ የድጋፍ ሰልፎች እና ህዝባዊ ተሳትፎ የተሞላ ሁነቶች ተከብሮ ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *