ቀጣዮቹ 90 ቀናት የአምስት ዓመቱ ዕቅድ አፈጻጸም የሚለካባቸው ወሳኝ ምዕራፍ በመሆናቸው በልዩ ትኩረት ሊመሩ ይገባል፦ ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የመንግሥት እና የብልፅግና ፓርቲ የተግባር አፈጻጸም በቦንጋ ከተማ ገምግሟል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ቀጣዮቹ ዘጠና ቀናት በአምስት ዓመቱ ለህዝቡ የተገባ ቃል አፈጻጸም የሚመዘንበት በመኾኑ በልዩ ትኩረት ሊፈጸም እንደሚገባ አሳስበዋል።

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በክልሉ በሁሉም መስኮች ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የጠቆሙት።

በቀጣይ የተጀማመሩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ልዩ ትኩረት ተደርጎ መጠናቀቅ እንዳለበት ያሳሰቡት ዶ/ር ነጋሽ ፤የመኸር ማሳ ዝግጅት በተደራጀ መልኩ መፈጸም አለበት ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው፣ የፓርቲውን የአደረጃጀት መዋቅር ይበልጥ በማጠናከር የላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት ያላቸው ግንባር ቀደም አባላትን ማፍራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በየደረጃው ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ያስገነዘቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የግብር ስርዓት ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ መሸፈን ይገባል ብለዋል።

መደበኛ የማኅበራዊ ዘርፍ ተግባራት ክትትልና ድጋፍ ማጠናከር እንደሚገባ ያስታወቁት ዶ/ር ነጋሽ፤ በየደረጃው ሠላም የማጽናትና የፀጥታ መዋቅር ማደራጀት ተግባራትን በትኩረት ማከናወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ 7ተኛ ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍጹም ሠላም ሆኖ እንዲጠናቀቅ አመራሩ ሚናውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በክልሉ የተመዘገቡ ስኬቶች በአመራሩ ቁርጠኝነት የተገኙ መሆናቸውን የጠቀሱት የክልሉ መንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን፤ በቀጣይም የተሻሉ ውጤቶችን ለማስመዝገብ የአመራር ቅንጅቱ ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።

አመራሩ በርካታ ተግባራትን በአንድ ጊዜ የመፈጸም አቅሙን እያሳደገ መምጣቱን የገለጹት አቶ ፍቅሬ፤ ይሁን እንጂ በሁሉም እርከኖች ተግባራትን አሟጦ ከመፈጸም አኳያ የሚስተዋሉ መሠረታዊ ክፍተቶች መኖራቸውን አመላክተዋል።

የአመራሩ የክትትልና የድጋፍ ስርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱ የገለጹት አቶ ፍቅሬ፤ በቀጣይም በየደረጃው ያለው አመራር የፓርቲ መደበኛና የንቅናቄ አጀንዳዎችን በላቀ ቁርጠኝነት መፈጸም እንዳለበት በአጽንኦት ተናግረዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *