



የክልሉ መንግስትና የፓርቲ 9 ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የክልሉን መንግስት የ9 ወራት ስራ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት የክልሉ ፕላንና ልማትና ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ወሰነች ቶማስ በተለይ የኢኮኖሚ ክላስተር አፈፃፀሙን በዳሰሰው ሪፖርታቸው ግብርና የክልሉ ትልቁ ፀጋ በመሆን ዘርፉን በማሻሻልና በማዘመን የህብረተሰቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ላለፉት 9 ወራት ከ623 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ23 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማሰባሰብ መቻሉን ገልፀዋል። ምርታማነቱን ለማሳደግ በተለይ የአርሶ አደሮችን ግንዛቤ ማሳደግና የግብርና መካናይዜሽን ማስፋፋት ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቁመዋል።
በክልሉ የኩታገጠም እርሻዎች አፈፃፀም እያደገ በመምጣቱ ከ85 ሺህ ሄክታር በላይ በኩታ ገጠም የለማ ስሆን ከዚህም ውስጥ ከ14 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በሜካናይዜሽን እርሻ ስርዓት የለማ መሆኑን ጠቁመዋል።
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የወጪ ምርቶችን አቅም ለማሳደግ ከመሄርና ከበልግ እርሻ ስርዓት በተጨማሪ የበጋ መስኖ ተግባራዊ በመደረጉ የምርታማነት መጠኑን ወደ 35 ኩንታል ማሳደግ ተችሏል ብለዋል። በዚህም እስከአሁን ከ5000 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የበጋ ስንዴ በማልማት እስከአሁን 154 ሺህ ኩንታል ምርት ማሰባሰብ ተችሏል ብለዋል።
በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ የዶሮ፣ የወተት፤ የእንቁላል፣ የቀይ ስጋና የዓሳ ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እንደተቻለም ገልፀዋል። እንስሳት የክልሉ አንዱ ፀጋ በመሆኑ ምርታማነቱን ለማሳደግ የዝርያ ማሻሻያ የመኖ ዝግጅት የትኩረት አካል እንደሆነ ነው የጠቆሙት።
ቡናና ቅመማ ቅመም የክልሉ ትልቁ ኢኮኖሚ መሰረት በመሆኑ ምርታማነትና የማሳ ሽፋንን ማሳደግ ላይ በተሰጠው ትኩረት ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን በመጠቆም በበጀት ዓመቱ የእስከአሁን አፈፃፀም ከ19400 ቶን በላይ የታጠበና 23,674 ቶን በላይ ያልታጠበ በጥቅሉ ከ48 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።
የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ለማስተዋወቅ በክልሉ የደን ሽፋንን 43% ለማድረስ እንደተቻለ የጠቆሙት ሀላፊዋ በክልሉ 856 ሺህ ሄክታር በላይ ደን ከካፋ ዞንና ከሸካ ዞን በዩኔስኮ በባዮስፌር ሪዘርቭ የተመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ የእስከአሁን አፈፃፀም ከ57 ሺህ በላይ ወጣቶች ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠር የተቻለ ስሆን ከዚህም ውስጥ 41% የሚሆነው በግብርና ዘርፍ የተገኘ የስራ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ አንስተኛ መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት የወጪና ተኪ ምርቶችን ለማቅረብ በተሰራው ስራ እስከአሁን 144 የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ወደስራ ማስገባት ተቿሏል ብለዋል። በእነኝህ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ከተመረቱ ምርቶች 4.3 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ነው የገለፁት። ተኪ ምርቶችን በማልማት ከ42 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ማትረፍ እንደተቻለም ጠቁመዋል።
በንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ በበጀት ዓመቱ እስከአሁን 9.2 ቢሊዮን ብር ላስመዘገቡ 45 ሺህ ነጋዴዎች ፍቃድ መሰጠት እንደተቻለ ገልፀዋል
ሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን ለመከላከል በተወሰደው እርምጃ በተለይ በህገወጥ መንገድ ስንቀሳቀስ የነበረው ቡናና ነዳጅ ተይዞ ለመንግሥት ገቢ መደረጉን ገልፀዋል። በዚህም ወደ 24.8 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ መደረጉን ጠቁመዋል።
በክልሉ በግብርና በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፍላጎት እያደገ በመምጣቱ 5.5 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ 93 እንቨስተሮች ፍቃድ መውሰዳቸውን ገልፀዋል።
የክልሉን የወጪ ፍላጎት በገቢ ለመሸፈን ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ ወሰነች በጀት ዓመት 14 .2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እስከአሁን 12.6 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ እንደተቻለ ጠቁመዋል። የተጀሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ የገቢ አቅሞችን ለይቶ መሰብሰብ ትኩረት ልደረግ እንደሚገባም ጠይቀዋል።
በንጉሴ ወልደየስ
