




በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 302 ነጥብ 27 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረቡን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።
ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ወልያብ (ዶ/ር) እንደገለጹት ኤጄንሲው በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 262 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ ታቅዶ አፈጻጸሙ ከዕቅዱ በላይ ማሳካት መቻሉን አንስተዋል።
በዚህም ከክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 302 ነጥብ 27 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ መቻሉንነው ያስታወቁት።
ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበውን ወርቅ ለማሳደግ በተሰራው ስራ ቀደም ሲል የነበረው የአምራች ማህበራት ቁጥር መጨመሩ ለውጤቱ መገኘት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል።
የክልሉ የወርቅ ምርት መጠን እየተሻሻለ ማምጣቱ የክልሉን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት አይነተኛ ሚና እየተጫወ መሆኑን ገልጸዋል ።
በወርቅ ግብይቱ ይስተዋሉ የነበሩ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል ግብይቱ በተደራጁ ማዕከላት ብቻ እንዲከናወን መደረጉንና የቁጥጥር ሥራውን የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል መደረጉን አንስተዋል።
የክልሉን የወርቅ ምርት ከዚህ በላይ የማሳደግ አቅም እንዳለ አመላካች ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸው ዘርፉ በልዩ ትኩረት እየተመራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከአዳዲስ ፍቃድ እና ነባር የማዕድን ዘርፍ ፈቃዶች እድሳት ከ124 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል 150 ሺህ ቶን ድንጋይ ከሰል ለማምረት ታቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 122 ሺህ ቶን በላይ ድንጋይ ከሰል ማምረት መቻሉን ገልጸዋል።
573 ሺህ 134 ሜትር ኪዩብ የኮንስትራክሽን ግብአት ተመርቶ ለአገልግሎት መብቃቱን አብራርተዋል ።
በዚህም ከ10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ከ40 ነጥብ 5 ሚልየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት 113 የማዕድን ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ 202 የማዕድን ፈቃዶችን በመስጠት ከዕቅድ በላይ ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።
በተከተል ወ/ሚካኤል
