




በሰዓሊ አብረሃም ተስፋዬ የተዘጋጁና የካፋን ነገሥታት ታሪክ፣ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓትና የማኅበረሰቡን ጥንታዊ አኗኗር የሚዘክሩ የስዕል አውደርእይ በቦንጋ ከተማ ተከፍቷል።
የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ትናንትን፣ ዛሬንና ነገን አሰናስነው የሚይዙ በመሆናቸው ለማኅበረሰብ የታሪክ ዕድገት ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ነው በአውደርዕይ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው የገለጹት።
ኪነ-ጥበብ የአንድን ማኅበረሰብ ቱባ ባህል፣ ዕሴት እንዲሁም ታሪክ በማቀናጀት ገዥ ትርክት በመገንባት ለሀገር መንግሥት ግንባታ የጎላ ፋይዳ እንዳለውም ነው አቶ ማስረሻ የገለጹት።
በሰዓሊ የቀረቡ ሥራዎች በታሪክ የሚወሱ የጥንት የካፋ ማኅበረሰብ ፍንትው አድርጎ ያሳየ እንደነበረ የገለጹት አቶ ማስረሻ፣ ይህም በትውልድ ቅብብሎሽ ታሪክን በተሻለ መልኩ ለመዘከር የሚረዳ ነው ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በርካታ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሀብቶች የበለጸገ መኾኑን የገለጹት አቶ ማስረሻ፤ እነዚህን ፀጋዎች ከሳች በኾነ መልኩ በኪነጥበብ ሥራዎች ማጉላት የክልሉን የቱሪዝም ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በበኩላቸው፣ ከነ ጥበብ በአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የዜጎችን አስተሳሰብና አመለካከት በመቅረጽ፣ የጋራ ራዕይን የሚፈጠር እንደኾነ ተናግረዋል።
ኪነጥበብ በአዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ውስጥ ትኩረት የተሰጠው እንደኾነ የገለጹት አቶ አልማው፤ በዚህም ከታችኛው የትምህርት ደረጃ ጀምሮ ዜጎች ያላቸውን ተሰጥዖ በተገቢው እንዲያዳብሩ ዕድል የፈጠር እንደኾነ ገልጸዋል።
በመደመር መንግሥት እይታ ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት በተሻለ መልኩ ዘርፉን ለማሻገር የሚረዳ እንደኾነ የገለጹት አቶ አልማው፣
የመንግሥት ተቋማትና ግልሰቦች በሰዓሊው የተዘጋጁ የስዕል ስራዎችን በመግዛት በማበረታታት ለቀጣይ ስራው ተጨማሪ አቅም መፈጠር ይገባል ብለዋል።
ሰዓሊ አብርሃም ተስፋዬ በበኩሉ፣ ያቀረባቸው ስዕሎች ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ያለውን የካፋ ማኅበረሰብ ታሪክ፣ ባህልና ተፈጥሯዊ ሀብቶች የሚያንጸባርቁ መሆናቸውን ገልጿል።
በቀጣይ የስዕል ስራዎቹን በስፋት ለተመልካች የማድረስ ዕቅድ እንዳለው የገለጸው ሰዓሊ አብርሃም በተላይም ከማሳያ ቦታ ጋር ያለውን ችግር መንግሥት እንዲፈታለት ጠይቋል።
የማኅበረሰብ ታሪክና ባህል ማስተዋወቅ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ሥራ ባለመኾኑ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ መጠናከር እንዳለበትም ሰዓሊው ተናግረዋል።
በቦንጋ ብሄራዊ የቡና ሙዚየም የተከፈተውን የስዕል አውደርእይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየጎበኙ መኾኑም ተመላክቷል።
በዕድገቱ በዛብህ
