ኅብረ-ብሄራዊ አንድነትን የሚፈታተኑ የፊውዳል አስተሳሰቦችን በጽናት መታገል ይገባል” – ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን፤ በሞዲዮ የፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም ያሰለጠናቸውን የ1ኛ ዙር መደበኛ ፖሊስ አባላትን ዛሬ በደመቀ ሁኔታ አስመርቋል።

በምረቃው መርሃ-ግብር ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ለተመራቂዎቹ የሥራ መመሪያ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፤ ተመራቂ ፖሊሶች ሙያዊ ሥነ-ምግባርን በመጠበቅ የፍትሕ መከበርን እንዲያረጋግጡ አሳስበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ተመራቂዎች የተጣለባቸውን ሕዝባዊ አደራ በመወጣት ሕገ-መንግሥቱንና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከማንኛውም ጥቃት የመከላከል ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። አክለውም ” ኅብረ-ብሄራዊ አንድነትን የሚጻረሩ የፊውዳል አስተሳሰቦችን በጽናት መታገል ይገባል” ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት የጸጥታ መዋቅሩን መልሶ በማደራጀት ሕዝባዊ ኃላፊነቱን በብቃት እንዲወጣ በቁርጠኝነት ሲሠራ መቆየቱን የገለጹት ዶክተር ነጋሽ፤ በዚህም ተጨባጭና የተሻሉ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ መላው የክልሉ ማኅበረሰብ ድርሻውን እንዲወጣ ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ፤ ተመራቂዎች በሥልጠና ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ፣ የሕዝቡን ደኅንነት የመጠበቅና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነታቸውን በታማኝነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ካሣ በበኩላቸው፤ የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት በዘላቂነት ለማስጠበቅ በዕውቀትና በተግባር የሰለጠነ ብቁ የፖሊስ ኃይል መፍጠር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ኮሚሽነር ዶክተር ካሣ ገለጻ፤ ተመራቂ ፖሊሶቹ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በዕጣ ተመድበው ወደ ሥራ የሚሰማሩ ይሆናል።

ይህ የስምሪት ሥርዓት የፖሊስ ኃይል በሁሉም አካባቢዎች በፍትሐዊነት እንዲሰማራ፣ ፖሊሶች የሕዝብን አደራ በገለልተኝነት እንዲወጡና በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ያለመ እንደሆነም ተጠቁሟል።

በተቋሙ ታሪክ የመጀመሪያው የሆነው ይህ የምልምል ፖሊሶች ሥልጠና በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ኮሚሽነር ዶክተር ካሣ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *