‎የ2018 ዓ.ም የሸካ ዞን እግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና ዉድድር በቴፒ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

Spread the love

‎ከሚያዝያ 08/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 8 ቀናት ሲካሄድ የቆየዉ የ2018 ዓ.ም የሸካ ዞን እግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና ዉድድር ፍፃሜውን አግኝቷል ።

‎በዉድድሩ መዝጊያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተዉ ንግግር ያደረጉት የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ ስፖርት በስነ ምግባር የታነፀ፣ በአካል የዳበረ ፣በአዕምሮ የበለፀገ፣ በህብረ ብሄራዊ ኢትዮጵያዊነት የሚያምን ዜጋን ለመፍጠር ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልፀዉ ለዉድድሩ አሸናፊዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸዉን አስተላልፈዋል።

‎ዞኑ ለስፖርቱ ልማት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የገልፁት ዋና አስተዳዳሪዉ በቀጣይ ዞኑን ወክለው በክልል አቀፍ መድረክ ላይ የሚሳተፉ ቡድኖች ውጤት እንደምያስመዘግቡ እምነታቸውን ገልፀዉ ቴፒ ከተማ የዘንድሮዉን የ2018 ዓ.ም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የእግር ኳስ ሻምፒዮና እንድታዘጋጅ መመረጧን አብስረዋል።

‎ውድድሩ ከዓላማዉ አንፃር ግቡን ያሳካ እንደነበር የገለፁት የሸካ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጀመረ ተሰማ ውድድሩ ከፍተኛ ፉክክር የታየበት መሆኑ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እድል የከፈተ ነው ብለዋል ።

‎በዙር በተካሄደዉ የዘንድሮ ሻምፒዮና ቴፒ ከተማ 8 ነጥቦችን በመሰብሰብ መሪነቱን ይዞ ስያጠናቅቅ የኪ ወረዳ በ6 ነጥቦች ተከታዩን ደረጃ በመያዝ አጠናቋል።

‎የዉድድሩ ኮከብ ተጫዋች ላክደር ጌታቸዉ ፣ከፍተኛ ግብ አግቢ መሀመድ ሰይድ፣ ኮከብ አሰልጣኝ ምስጥሩ ሲሳይ ሲሆን ሀብታሙ ተገኝ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሁኖ ተመርጠዋል።

‎በመጨረሻም ለዉድድሩ አሸናፊ የዋንጫ እና ሜዳልያ ሽልማት የተሰጠ ሲሆን ሻምፒዮናዉ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ አስተዋጽኦ ላደረጉት አካላትም የምስክር ወረቀት በመስጠት ውድድሩ ተጠናቋል ሲል ማሻ ኤፍኤም ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *