




ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ከ346 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለሚገነባው ሆስፒታል የመሠረተ ድንጋይ አኑረዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ፥ በዳውሮ ዞን ኢሰራ ባሌ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ መሠረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።
ከ346.8 ሚሊዮን ብር በሆነ የክልሉ መንግሥት በመደበው በጀት ወጪ የሚገነባውን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአግልግሎት ክፍት እንደሚሆን ተጠቁሟል።
የሆስፒታሉ መገንባት ከዚህ ቀደም ከህብረተሰቡ የሚነሳውን የልማት ጥያቄን ከመመለስም ባሻገር የጤና አገለግሎት ሽፋንና ጥራት የሚያሳድግ፤ የእናቶች እና ህፃናት ሞት ለመቀነስ ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ገልጸዋል።
በመርሐ-ግብሩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸውን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የአከባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በጌታሁን ግርማ
