




ኢትዮጵያ እና አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችል ምክክር በዋሽንግተን ዲሲ አካሂደዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የተመራውና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ፣ የብሄራዊ ደኀንነትና መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንን ያካተተ ልዑክ ከአሜሪካ አቻዎቹ ጋር ተወያይቷል።
ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ያካሄዱት የሁለትዮሽ መዋቅራዊ ምክክር በሦስት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ሲሆን፤ ይኸውም የኢኮኖሚ ብልጽግናን፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት፤ የመከላከያ እና ጸጥታ፤ እንዲሁም ቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት ማስፈንን የተመለከተ ነው።
ይህ የሁለትዮሽ መዋቅራዊ ምክክር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ዘላቂ በሆነ መንገድ የሚያስቀጥልና የሚያጠናክር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
