






በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የምርጫና ሌሎች ንቅናቄ አጀንዳዎች አፈጻጸም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል።
በመድረኩ ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት፤ አመራሩ የምርጫና ንቅናቄ አጀንዳዎችን በተቀመጠው አሰራር ሥርዓት መሠረት በኃላፊነት መምራትና መፈጸም እንደሚገባው አሳስበዋል።
በተለይም የምርጫ ሂደቶችና ሌሎች የንቅናቄ ሥራዎች በቅንጅትና በተጠናከረ አመራር እንዲከናወኑ ሁሉም የአመራር አካላት የድርሻቸውን በብቃት እንዲወጡ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
የምርጫ ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረገው በጋራ የመሥራት ልምዱ እንደሚጠናከርም ርዕሰ መስተዳድሩ አንስተዋል።
ከምርጫ ሥራ ጎን ለጎን የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት አጀንዳዎች በልዩ ትኩረት መመራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን፤ በክልሉ እየተካሄደ ያለው የአመራር ድጋፍና ክትትል ሥራ በመንግሥትና በፓርቲ የሚመሩ አጀንዳዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ፍቅሬ አማን በየጊዜው የሚደረጉ የድጋፍና ክትትል ሥራዎችን መገምገምና የተጠናከረ የመረጃ ሥርዓት መፍጠር በየዘርፉ ውጤቶች እንዲመዘገቡ እያስቻለ ነውም ብለዋል።
በተጨማሪም ከጊዜ ወደ ጊዜ የአመራሩ በፓርቲና መንግሥት የተቀመጡ አቅጣጫዎችን የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል።
ሆኖም በአንዳንድ መዋቅሮች የሚስተዋሉ የተግባራት አፈጻጸም ያለመጣጣም ችግሮች አሁንም መኖራቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህን ችግሮች መቅረፍ “ለነገ” የሚባል ጉዳይ እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።
አመራሩ የምርጫና ሌሎች የንቅናቄ አጀንዳዎችን በልዩ ትኩረት መምራት እንደሚጠበቅ የገለጹት አቶ ፍቅሬ አማን የቀጣይ የአመራር የሥራ ሥምሪት ዛሬ በሚመዘገበው ውጤት ልክ እንደሚወሰንም አስታውቀዋል።
በፍቅር ከበደ
