




በቤንች ሸኮ ዞን የመንግስትና የፓርቲ ተግባራት አፈፃፀም እንዲሁም የ7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ግምገማ የክልል ደጋፊ አካላትና ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በዛሬው ዕለት እየተካሄደ ይገኛል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን ወቅቱ አመራሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት እንዲፈጥር የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።
የእስካሁኑ የምርጫ ቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በመገምገም በጥንካሬ የታዩትን በማስቀጠልና ድክመቶችን በአፋጣኝ በማረም ቀጣይ ስራዎችን በቁርጠኝነት መፈፀም እንደሚገባ አሳስበዋል።
አቶ ፍቅሬ በንግግራቸው የ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሁለት ዋና ዋና ስኬቶችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊና በሁሉም ዘንድ ተአማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ ማድረግ እና በሂደቱ የብልፅግና ፓርቲ በህዝብ ድምፅ አብላጫ ድምፅ እንዲያገኝ ማስቻል ነው ብለዋል።
ሌላው አሁን ያለው ሀገራዊ፣ ቀጠናዊና አለም አቀፋዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች እንዲሁም ያሉ ጫናዎች ምርጫውን ካለፉት ጊዜያት የተለየ እንደሚያደርጉት የገለጹት ኃላፊው ቀድመን በመጣንበት መንገድ ሳይሆን አሁን ያለው ሁኔታ በሚፈልገው የትግል አግባብ መከናወን አለበት ብለዋል።
በዞኑ በሚገኙ የምርጫ ክልሎች ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ምቹ የውድድር ሜዳ መኖሩን ጠቅሰው ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በምርጫ ህጉ መሰረት ፍጹም ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በመድረኩ እየተገመገሙ ካሉ ዋና ዋና ነጥቦች መካከል የመንግስትና የፓርቲ የንቅናቄ አጀንዳዎች አፈፃፀም፣ የመልካም አስተዳደር ኢኒሼቲቭ ስራዎች ያሉበት ደረጃ፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ ያሉ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች ይገኙበታል።
ይህ የግምገማ መድረክ አመራሩ የተቀመጡ መርሆዎችንና የንቅናቄ አጀንዳዎችን በተገቢው ልክ እንዲፈፅም አቅጣጫ በማስቀመጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል ሲል የዞኑ ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
