




በካፋ እና በጅማ ሕዝቦች መካከል ያለውን ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ገለጹ።
ኃላፊው ይህንን ያመለከቱት በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘውና በሁለቱም ወንድማማች ዞን ህዝቦች መካከል በተደረገው የባህል ምክክር መድረክ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው።
የካፋ እና የጂማ ሕዝቦች ታሪክ “ከአንድ ወንዝ የተቀዳ” መሆኑን በመጥቀስ፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ዘመናትን የተሻገረ የማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ ትስስርን ይበልጥ ማጠናከር ወቅታዊና ወሳኝ ተግባር መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም፣ የሁለቱም ዞኖች ሕዝቦችና የሀገር ሽማግሌዎች ያላቸውን ታሪካዊ ትስስር በ”መደመር እሳቤ” ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ትውፊትና የጠነከረ የጋራ መስተጋብር ያላቸውን የእነዚህን ሕዝቦች አንድነት ይበልጥ መገንባት እንደሚገባም አሳስበዋል ።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ሁለቱ ሕዝቦች በደም፣ በጋብቻ፣ በባህልና በጂኦግራፊ የተሳሰሩ መሆናቸውን ገልጸው በቀጣይም ይህንን ሁለንተናዊ ግንኙነትና ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል ።
የካፋ ዞን የሚኪሬቾ ስርዓት እና ሌሎች ውብ እሴቶች ባለቤት መሆኑን ገልጸው ማህበራዊ መስተጋብርን በሚያጠናክሩ በበጸጥታ እና መሰል ጉዳዮች ላይ ያሉ ግንኝነቶችን ማጠናከር ወሳኝ ነው ብለዋል።
የጂማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው የሁለቱን ህዝቦች አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር ለተደረገው ወንድማዊ አቀባበል አመስግነዋል ።
በቀጣይም በጅማ ዞን መሰል የህዝብ ለህዝብ ትስስር መድረክ ይደረጋል ሲሉ ገልጸዋል ።
በፕሮግራሙ የካፋ ንጉስ ኮላ ዎቾና የሚኪሬቾ አባላት የጂማ ዞን የሃገር ሽማግሌዎች ፣ የሀይማኖት አባቶች እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል ሲል ቦንጋ ኤፍ ኤም 97.4 ዘግቧል ።
