Trendings

ገጠሪቱን ኢትዮጵያ የማበልጸግ ራዕይ ከመሠረተ ልማት ዝርጋታ እስከ አህጉራዊ የሀብት ፈጠራ እና ዘመናዊነት

Spread the love

የመደመር መንግሥት ገጠሪቱን የኢትዮጵያ ክፍል የምግብ ዋስትና የተረጋገጠባት፣ የዘመናዊነት፣ የሀብት ፈጠራ እና የምቹ መኖሪያ ማዕከል የማድረግ ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ ሰንቆ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴዎችን በማካሄድ ላይ ይገኛል።

ይህ ጥረት ባህላዊውን የግብርና አሠራር ወደ ዘመናዊና ምርታማ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከማሸጋገር ባለፈ፣ የገጠሩን ማኅበረሰብ የኑሮ ደረጃ በዘላቂነት ለማሻሻል ያለመ ነው።

አርሶ አደሮች መሬታቸውን በኩታ ገጠም በማስተባበር የትራክተር፣ የኮምባይነር እና የዘመናዊ መስኖ ቴክኖሎጂዎችን አጠቃቀም በማሳደግ ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምሩ ተደርጓል።

በተለይም በበጋ ስንዴ ልማት የተመዘገበው ታሪካዊ ስኬት ሀገራችንን ከስንዴ ጥገኝነት ነፃ ከማውጣቱም በላይ ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ አቅም በመፍጠር የአርሶ አደሩን ገቢ በእጥፍ ያሳደገ አዲስ የኢኮኖሚ ምዕራፍ ከፍቷል።

የገጠር ኮሪደር ልማትን በመተግበር እና መሠረተ ልማት ሥራዎችን በማስፋፋት የገጠር መንገዶችን፣ የመጠጥ ውኃ እና የኤሌክትሪክ አቅርቦትን በማሳደግ አርሶ አደሩ ምርቱን በቀጥታ ወደ ማዕከላዊ ገበያ የሚያቀርብበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መንግሥት እየተገበረ በሚገኘው የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ በየአካባቢው የዶሮ፣ የንብ፣ የከብት ማደለብ እና የወተት ምርት ተግባራትን በማስፋፋት የገጠሩ ማኅበረሰብ የምግብ ዋስትና ከመረጋገጡም በላይ ተጨማሪ የሀብት ምንጭ እንዲፈጥር አስችሏል።

በተመሳሳይ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች ከተፈጥሮ እንክብካቤ ባሻገር የአቮካዶ፣ የፓፓያ እና የማንጎ ችግኞችን በመትከል አርሶ አደሩ ከአትክልትና ፍራፍሬ አዲስ የገቢ መስመር እንዲያገኝ ተደርጓል።

በተጨማሪም የሞዴል መንደሮች ግንባታን በማከናወን ገጠሪቱ የሀገራችን አካባቢ የተሟላ የአገልግሎት ማዕከል እንዲሆን የገጠር መኖሪያ ቤቶችን ማሻሻል እና ደረጃቸውን የጠበቁ የሕዝብ አገልግሎቶችን የማቅረብ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በዚህም በገጠር ለሚኖሩ ወጣቶች በግብርና ምርት ዝግጅት፣ በማጓጓዝ እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የገበያ ትስስር ላይ እንዲሰማሩ በመደገፍ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።

ይህ የተቀናጀ ጥረት ገጠሪቷ ኢትዮጵያ ምርት የሚመረትባት ብቻ ሳትሆን፣ ዘመናዊ ኑሮ የምታይባት እና ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ዋና የሀብት ምንጭ የምትሆንበትን አዲስ ምዕራፍ እያረጋገጠ ይገኛል።

#EBC

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *