
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ በፌዴራል ደረጃ እንዲሁም በዲያስፖራው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ የሚሳተፉ ወኪሎች ከየባለድርሻ አካላቱ ሲያስመርጥ መቆየቱ ይታወሳል።
በዚህም መሰራት የተወከሉት ተመካካሪዎች በተዘጋጀላቸው ማረፊያ ቦታዎች እየገቡ የሚገኙ ሲሆን በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ሲደርሱም ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ተመካካሪዎች እጅግ መሠረታዊ በሆኑ እና በተለዩ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በጋራ ለመምከር ዕድሉን ማግኘታቸው ትልቅ አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለጉባኤው ስኬታማነትም የበኩላቸውን አዎንታዊ ሚና እንደሚወጡ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።
ለታሪካዊው ምክክር ስኬት ተመካካሪዎች አንዱ የሌላውን ሐሳብ በትዕግሥት ማዳመጥ እና ለመረዳት መሞከር እንደሚያስፈልግም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል።
“የእኔ ሐሳብ ብቻ ይቅደም” ከሚል ግትር አመለካከት በመላቀቅ የራስን ሐሳብ በሰለጠነ መንገድ ማስረዳት እንዲሁም የሌላውንም ወገን አመለካከት በመቀበል ለሀገራዊ መግባባት መፈጠር ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚጠይቅም ተመካካሪዎቹ አጽንኦት ሰጥተዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል
