



በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሸካ ዞን፤ ቴፒ ከተማ 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በማስመልከት ብልፅግና ፓርቲውን የሚደግፍ እና የይምረጡን ምርጫ ቅስቀሳ ታላቅ ሕዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት አካታች የፖለቲካ ስርዓት በመዘርጋት ሀገር በቀል በሆነው የመደመር እሳቤ የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ ተግባራትን ወደ ውጤት በመቀየር ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል።
በዚህም የፖለቲካ አካታችነትን፣ ፍትሃዊ ልማት ተጠቃሚነትን፣ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን ደረጃ በደረጃ የምንመልስበትን ትልቅ እና ሰፊ አውድ መፈጠሩን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት።
እንደክልል በእኩል የምንደመርበት፣ ጥያቄዎቻችን በሰላማዊ መንገድ የምናቀርብበት፣ በሃሳብ የበላይነት ልንሟገት የምንችልበት ምቹ ሁኔታዎች መፈጠሩን ነው ያነሱት።
በክልላችን ብሎም እንደሸካ ዞን ባለፉት ጊዜያት የሚነሱ የሰላምና የልማች በመደመር እሳቤ በመመራት ህዝቡን በማስተባበር መጠነ ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውን ነው የተናገሩት።
በዞኑ የመጣውን አስተማማኝ ሰላም በትብብር በማስቀጠል በአከባቢውን ያለውን እምቅ ሀብቶች ወደ ውጤት እንዲቀየር ፓርቲውና የክልሉ መንግሥት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በማከልም በፓርቲው መሪነት የመጡ ለውጦች እንዲቀጥሉና ቀጣይ የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲፈቱ ብልጽግና ፓርቲ እንዲመርጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን፣ የቀደሙ ስርዓቶች የሀገሪቱን መሰረታዊ ችግሮች በአግባቡ መፍታት ባለመቻላቸው ኢትዮጵያ ለዘመናት በጦርነትና በኋላ ቀርነት ውስጥ መቆየቷን አስታውሰዋል።
መጋቢት 24 የመጣው የለውጥ አመራር ሀገርን ከብተና በማዳን በተለያዩ ዘርፎች ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ መቻሉን ነው የገለፁት።
ፓርቲው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እንዲመሰረት በማድረግ የሕዝቡን የራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ መመለሱንም ገልጸዋል አቶ ፍቅሬ አማን።
በፓርቲው መሪነት በሸካ ዞን ገጠር መንገዶች፣ የአስፋልት መንገዶች፣ ሆስፒታሎች፣ የኤሌክትሪክ ሳብ-ስቴሽን፣ ንፁህ ውሃና የመስኖ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የትምህርትና የጤና ተቋማት ልማት መከናወኑን ገልፀዋል።
ሆኖም ሁሉም የሕዝብ ጥያቄዎች አልተፈቱም ያሉት አቶ ፍቅሬ፣ ቀጣይ አምስት ዓመታትም ከሕዝብ ጋር በመመካከር ቀሪ ችግሮችን ለመፍታት ፓርቲው በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በበኩላቸው፣ ብልፅግና ፓርቲ በኢትዮጵያ ታሪክ በሰላማዊ መንገድ ወደ ስልጣን የመጣ ትልቅ ፓርቲ መሆኑን ገልፀዋል።
በዞኑ ባለፉት ዓመታት በፓርቲው መሪነት የሰላምና ጸጥታ ስራዎች፣ የቴፒ አውሮፕላን ማረፊያ ደረጃ ማሻሻያ ማሻሻያ፣ የመብራት፣ የመንገድና የንፁህ ውሃ ፕሮጀክቶች በለውጡ ዘመን ከተከናወኑ ዋነኛ ስራዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በፍቅር ከበደ
