የኮንታ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ ህንግጫ በዓል ጳጉሜ 2/2018 ዓ.ም በታላቅ ድምቀት በአመያ ከተማ ይከበራል።

እንኳን ለኮንታ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ ህንግጫ በዓል በሰላም አደረሳችሁ/አደረሰን “ህዮዋ ህዮዋ ባላ ህዮዋ”
ክረምቱ አልፎ፣ ሰማዩ ጠርቶ፣ አዲስ ዓመት ሲበሰር፤ የኮንታ ብሔር ከትውልድ ወደ ትውልድ ያስተላለፈውን ጥንታዊ የዘመን መለወጫ በዓል “ህንግጫ” በዓልን በደማቅ ባህላዊ ድምቀት ያከብራል።
ኮንታ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ባለቤት ነው። ከእነዚህ ውብ የማንነት መገለጫዎች መካከል ህንግጫ አንዱ ነው።
ህንግጫ በብሔረሰቡ ዘንድ በየዓመቱ በታላቅ ድምቀት የሚከበር የብሔሩ ዘመን መለወጫ በዓል ሲሆን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሻገር ከነሙሉ ክብሩ ነው፡፡ እሴቱ ሳይጎድል ውበቱ ሳይደበዝዝ እዚህ የደረሰ የብሔረሰቡ የማንነት መገለጫ ነው፡፡
የኮንታ ህዝብ የዘመን መለወጫ በዓል ማክበር የጀመረዉ በኦሞ፣ በጎጀብ እና በዝግና ተፋሰስ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው።
በኮንታ መንግሥት ተመስርቶ ግዛቱን ተቆጣጥሮ መኖር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ማለትም የመጀመሪያው የአራ የዘረ-ግንድ ቀዳሚ ንጉስ “ከካቲ ኤማዶ” ዘመነ መንግስት በ12ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ይበልጥ በተጠናከረ ሁኔታ በቤተሰብ ደረጃም ሆነ ከጎረቤት ጋር በጋራ በመሆን በዓሉን እያከበሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው።
“ህንግጫ” በኮንታ ባህላዊ አጠራር ያማረ፣ ያጌጠና የለመለመ ማለት ሲሆን፣ አደይ አበባ በሚፈካበት፣ የክረምቱ ዝናብ አልፎ ጠራ ሰማይ በሚታይበት እና አርሶ አደሩ የወቅቱን የእርሻ ሥራ አጠናቆ ለመልካም ፍሬ ተስፋ በሚሰንቅበት ወቅት ይከበራል።
እንደ ባህሉ ትውፊት ህንግጫ ከጳጉሜ እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ ደምቆ ይቆያል፡፡
ህንግጫ የብሔረሰቡ ዘመን መለወጫ ብቻ አይደለም፤ የእርቅ፣ የይቅርታ፣ የመተሳሰብና የተስፋ መገለጫ በዓልም ጭምር ነው።
በበዓሉ ወደ አዲሱ ዓመት ቂምና በቀል ይዞ መሻገር እንደሌለበት በመታመን፣ የተጣሉት በሽማግሌዎች ፊት ይታረቃሉ፤ “ይቅር ለእግዚአብሔር” በመባባል ያለፈውን ቂም ይተዋሉ። ቤተሰብና ጎረቤትም በአንድ ማዕድ ተሰባስበው አዲሱን ዓመት በፍቅርና በአንድነት ይቀበላሉ።
የህንግጫ በዓል ሲከበር ከአሮጌው አመት ወደ አዲሱ አመት መሸጋገሪያ እንደመሆኑ በዕለቱ ሁሉም ጠግበው፣ ጎዶሎ ሞልቶ፣ያለው ለሌለው አካፍሎ የሚበላበት፣ ደሃ ከሀብታም የማይለይበት፣መጥፎ ነገር ሁሉ ቀርቶ መልካም መልካሙ እንዲሸጋገር ፈጣሪውን የሚለምንበት የጥጋብና ሙሉ የመሆን አስተምህሮ የሚገለፅበት የተስፋ በዓል ነው።
የበዓሉ ዝግጅትም ከቤትና ከደጃፍ ጀምሮ አካባቢን በማጽዳት ይጀምራል፤ የአሮጌው ዓመት እድፍና ጉድፍ ይጠረጋል፤ ቤትና አካባቢ ይዋባል። በዚህም ከአሮጌው ዓመት ክፉ ነገርን አስወግዶ አዲሱን ዘመን በንጽህና፣ በብሩህ ተስፋና በመልካም ምኞት የመቀበል እሴት ይገለጣል።
ህንግጫ ከ12 ዓይነት በላይ የኾነው የኮንታ ባህላዊ ምግብ ተዘጋጅቶ የሚቀርብበት የባህል አውድም ነው። በበዓሉ የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች ይቀርባሉ፤ ሽማግሌዎችም ለተሰበሰበው ማህበረሰብ ምርቃት ይሰጣሉ። የምርቃቱም መሠረታዊ መልዕክት የሰላም፣ የፍቅር፣ የጤና፣ የጥጋብና የአንድነት ምኞት ነው።
በበዓሉ የአሮጌው ዓመት ረሃብ፣ በሽታ፣ ጥላቻና ክፉ መንፈስ ከቤት እንዲወጣ፣ አዲሱ ዓመት ደግሞ በጤና፣ በሰላም፣ በፍቅር፣ በጥጋብና በበረከት እንዲመጣ ይመረቃል። በተለይም የምግብ፣ የውሃና የወተት ዕቃዎች ሞልተው እንዲያድሩ የሚደረግ ሲሆን ይህም የመብዛትና የጥጋብ ምኞትን ያመላክታል።
በህንግጫ በዓል ወጣቶች በባህላዊ ጨዋታና ዜማ የሚደምቁበት፣ ቤተሰቦች የሚሰባሰቡበት ፣ ጎረቤቶች የሚጠያየቁበትና ትውልድ ከትውልድ ጋር የሚገናኝበት የማህበረሰብ አንድነት መድረክ ነው።
ህንግጫ ያለፈውን ቂም የሚያጸዳ፣ የአሮጌውን ዓመት ክፉ ነገር የሚያስወግድ፣ አዲሱን ዓመት በፍቅር፣ በሰላም፣ በጥጋብና በተስፋ የሚቀበል የኮንታ ሕዝብ የማንነት በዓል ነው።
