





“ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የታርጫ ማዕከል የመንግስት ሰራተኞች አመራሮችና አባላት የመሠረታዊ ድርጅት ኮንፈረንስ በድምቀት ተካሂዷል።
በኮንፈረሱ የተሳተፉ የታርጫ ማዕከል የክልል ቢሮ አባላትና አመራሮች በባለፉት ሁለት አመት ከግማሽ የምርጫ ዘመን በብልፅግና ፓርቲ የተገኙ ውጤቶች ተጠናክሮ እንዲቀጥሉና ቀጣይ ግቦች እንዲሳኩ ሚናቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በክልሉ በግብርና ዘርፍ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድንና በመልካም አስተዳደር ዘርፎች አባላትንና መላው የክልሉን ህዝብ በማሳተፍ የተገኙ ውጤቶች አበረታች መሆኑን የገለፁ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፌ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች በትብብር ይሰራል ብለዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በበኩላቸው ፓርቲው በሰው ተኮር አገልግሎቶችና በሌሎች ዘርፍ ባከናወናቸው ተግባራት በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸው ገልፀው በቀጣይ በማህበራዊ ዘርፍ የህብረተሰቡን የጤና ሁኔታ ለማሻሻልና ፍትሀዊ የጤና አገለግሎት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራም አብራርተዋል።
ፓርቲው የህዝቡን ችግር ለመፍታት በየደረጃው የተጀመሩ የጋራ የውይይት መድረኮች የብልፅግና ፓርቲ የህዝብ ወገንተኝነትን በተግባር የሚያረጋግጥ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የሀገርቱን የፖለቲካ ስርዓትን ህብረብሔራዊ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን የገለፁ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደረሰ ገቲሳ በክልሉ የትምህርት ጥራትና ፍትሀዊነት ችግር ለመቅረፍ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክሮ ይቀጥላሉ ብለዋል።
እንደ ሀገር በተለያዩ ዘርፎች በተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን ያብራሩት የክልሉ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ቢሮ ሀላፊ አቶ ተስፋዬ እንዳሻው በሰላም ግንባታ ዘርፍ አባላትና አመራሮች ግንባር ቀደም ሚና ልወጡ ይገባልም ብለዋል።
ሴቶችን ማብቃት ሀገርን መገንባት ነው ያሉት የክልሉ ምክር ቤት የከተማና መሠረተ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ አሰገደች ወልደየስ ፓርቲው ሴቶችን በሁሉም ዘርፍ ለማብቃትና ለማሳተፍ የሰራው የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
የአባላትና የአመራር ቁርጠኛነት ማነስ፣ የክልሉ የበጀት እጥረት፣ የከተማና የገጠር መሬት ወረራ፣ የገበያ ንረትና የስራ ባህል ጠንካራ አለመሆን እንደ ማነቆ የተነሱ ጉዳዮች ናቸው።
የፖለቲካና የዴሞክራሲ ሰርዓተ ግንባታ፣ የሰላም ግንባታ፣ የበለፀገ ኢኮኖሚ ግንባታ ስራዎች እንዲሁም ሀገራዊ የምክክር መድረኩን ተግባራዊ ማድረግ ከፓርቲው አባላትና አመራር አካላት የሚጠበቅ የቀጣይ ጊዜያት ተግባር እንደሆነም ተገልጧል።
