በክልሉ ያለውን ሀብት በአግባቡ ማልማትና ማስተዳደር ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ፦ ዶክተር ፍጹም አሰፋ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያለውን ሀብት በአግባቡ ማልማትና ማስተዳደር ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለፁ ።

ዶክተር ፍጹም አሰፋ ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ሱፐርቪዥን ቡድን በክልሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በመጎብኘት የድጋፍና ክትትል ሥራ በማድረግ ላይ ናቸው።

ሚኒስትሯ እንደተናገሩት የምልከታው ዋና ዓላማ በክልሉ አጠቃላይ በልማት የታቀዱ ስራዎች ምን ደረጃ ላይ አለ በሚለው ድጋፋዊ ክትትል በማድረግ በዚያ ሂደት ውስጥ መልካም ተሞክሮዎችን በመቀመር ወዴሌሎች አካባቢ እንዲሰፉ እና ድክመቶች ካሉ በመገምገም ክፍተት ያለበትን ለማረምና ለመደገፍ ነው ብለዋል።

ለዚህም ባለፉት ሁለት ቀናትና ከዚያ በላይ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር የሱፐርቪዥን መግቢያ ውይይት በማድረግ ወደ 17 በሚሆኑ ነጥቦች ላይ ክልላዊ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ በማየት መሬት ላይ ምን እንዳለ ለመገምገም በክልሉ ካሉት 6 ዞኖች 4ዞኖችን በመምረጥ በቤንች ሸኮ ዞን፣በሸኮና በደቡብ ቤንች ወረዳ እንዲሁም በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ሱፐርቪዥን ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በጉብኝቱ በቤንች ሸኮ ዞን በደቡብ ቤንች ወረዳ በ2500 ሄክታር ሙዝ ክላስተር በአርሶ አደሮች በክላስተር ተደረጅተው እክስፖርት ስታንዳርድ ሙዝ በማምረት ላይ ያሉ መሆኑንም አስረድተዋል።

በክልሉ በአትክልትና ፍራፍሬ በሙዝ፣ በቡና እና በሰብል ምርት የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ግብርናው በጣም ጥሩ በሚባል አፈፃፀም የሚያሳዩ መሆናቸውን በመስክ ምልከታው ማየታቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ በቤንች ሸኮ ዞን ባለፉት ሶስት ዓመታት በፀጥታ ችግር ውስጥ የነበረ ሸኮ ወረዳ ፀጥታን ሙሉ በሙሉ በማረጋገጥ ፊቱን ወደ ልማት በማዞር ህዝቡን በማስተባበር የውስጥ ለውስጥ መንገድ መሠረተ ልማትና ከተማን በመስፋፋት አበረታች ሥራ እያከናወኑ መሆኑን አይተናል ብለዋል።

በተፈጥሮ ሀብት ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ሀብታም ከሚባሉት ክልሎች አንዱ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ በክልሉ ያለውን ሀብት በአግባቡ ማልማትና ማስተዳደር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።

በፈዴራል ደረጀ በክልሉ የተጀመሩ ቀሪ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሠራ መሆኑን ተናግረው ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች እንዲሳኩ የፌዴራል መንግሥት መታገዝ የሚገባቸውን ነገሮች በማገዝ ከክልሉ መንግሥት ጋር በትብብር የሚሠራ መሆኑን ጭምር ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በክልሉ በግብርና ዘርፍ የሰብል ምርትና ምርታማነትን ከማድረግ አንጻር አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን የተናገሩት ደግሞ የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ ናቸው።

በክልሉ በቡናና ፍራፍሬ እንዲሁም በማር ምርት የሚታወቅ ነው ያሉት ዶክተር ፍቅሩ ቡና ምርት ከናጥራቱም ብሆን ለሀገር ገበያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለው ክልል ስለሆነ መንግሥት ክልሉ ይህንን ፖቴንሸል በደንብ እንዲያወጣ ቡና ላይ ከአቅርቦትና ምክረ ሃሳብ በመደገፍና ልማቱ እንዲወጣ በመሠረተ ልማት ማስተሳሰር ይገበል ብለዋል።

በቤንች ሸኮ ዞን በደቡብ ቤንች ወረዳ የጃንቹ በክላስተር እየተመረተ ያለው የሙዝ ምርት የአርሶ አደሩን ኑሮ ከመቀየር ባለፈ በሀገር ኢኮኖሚውም ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደለው ገልጸዋል።

በጅምር ላይ ያለው የማር ምርት በብዛትና በጥራት በማምረት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *