



የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰሞኑን አጋጥሞት የነበረውን የአገልግሎት መቋረጥ ችግር አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ በባንኩ የደንበኞች የግል አካውንት ላይ የደረሰ ምንም አይነት ጉዳት አለመኖሩን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ይፋ አድርገዋል።
ባንኩ የውስጥ አሰራሩን ለማዘመን ሲያደርግ በነበረው ሂደት አርብ መጋቢት 6 ሌሊቱን ጤናማ ያልሆነ የገንዘብ እንቅስቃሴ እንደነበረ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ የተፈጠረው ክስተት ከሳይበር ጥቃት ጋር የተያያዘ አለመሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አርብ ለሊት ብቻ ከ490 ሺህ በላይ የገንዘብ ልውውጥ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን ይህ የገንዘብ ልውውጥ ጤናማ የሆነውንም እንደሚጨምር ጠቁመዋል፡፡
“ገንዘብ በተለያየ መንገድ ጤናማ ባልሆነ መልኩ ከባንኩ በማውጣት ላይ በዋናነት የተሳተፉት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ አብዛኞቹ የድርጊቱ ተሳታፊ ተማሪዎች በባንኩ በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት የወሰዱትን ገንዘብ እየመለሱ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የባንኩን ጥሪ ተቀብለው ገንዘቡን ተመላሽ ላደረጉ ተማሪዎች ባንኩ ምንም አይነት ክስ እንደማይመሰርትም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተደጋጋሚ በአገራት በሚደገፉ ትልልቅ ተቋማት ጭምር የሳይበር ጥቃጥ ሙከራዎች ቢያጋጥሙትም አስተማማኝ የሳይበር ደህንነት ያለው ተቋም በመሆኑ ሁሉንም ሲያከሽፍ መቆየቱን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡
የደረሰው ጉዳት ከባንኩ አጠቃላይ ሀብት አንፃር በጣም አነስተኛ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አቤ ሳኖ፤ የደንበኞች የግል አካውንት ላይ የደረሰ ምንም አይነት ጉዳት ባለመኖሩ ደንበኞች ምንም አይነት ስጋት ሊገባቸው እንደማይገባ አበክረዋል፡፡
የችግሩን መሰረታዊ መንስኤ እና ያስከተለው ጉዳት ለማወቅ ምርመራ በመካሄድ ላይ መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ዝርዝር መረጃ ምርመራው ሲጠናቀቅ ለህዝቡ ይፋ እንደሚደረግም አስታውቀዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
