



በሸማቾች መብት ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራ የኢትዮጵያ የሸማቾች መብት ጥበቃ ማህበራት ጥምረት በይፋ ተመስርቷል፡፡
ጥምረቱ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴዔታ አቶ እንዳለው መኮንን፣ የንግዱ ዘርፍ ባለድርሻ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከተማ ተመስርቷል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴዔታ አቶ እንዳለው መኮንን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ሸማቾች በግብይት ስርዓቱ ላይ ትልቁን ድርሻ ይዘው ቢገኙም መብቶቻቸው ግን እየተከበረ አይደለም፡፡
በከፈሉት ዋጋ ልክ ደህንነቱ እና ጥራቱ የተጠበቀ ተመጣጣኝ ምርትና አገልግሎት አያገኙም ነው ያሉት፡፡
ይህ ደግሞ የራሳቸውን አደረጃጀት ፈጥረው ለመብቶቻቸው በጋራ መታገል ባለመቻላቸው የመጣ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ሽማቾች መንግስት በአዋጅ ያስቀመጠላቸውን መብቶች በአግባቡ ለመጠቀም መደራጀት እንዳለባቸው ነው ሚኒስትር ዴዔታው የገለጹት፡፡
ለዚህም ሚኒስቴሩ በቀጥታ የሸማቾች መብት እንዲከበር ከሚሰራቸው ስራዎች ጎን ለጎን ጠንካራ አደረጃጀት እንዲፈጥሩ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አመላክተዋል፡፡
በዚህም በዛሬው እለት ከክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የኢትዮጵያ የሸማቾች መብት ጥበቃ ማህበራት ጥምረት በይፋ እንዲመሰረት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ዛሬ የተመሰረተው ጥምረት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሸማቾች በህግ የተሰጣቸውን መብት እንዲያውቁ እና በግብይት ሒደት የሚገጥሟቸውን የመብት ጥሰቶች በጋራ እንዲታገሉ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጥምረቱ ይህን ለማድረግ ከፍተኛ ሃላፊነት የተጣለበት መሆኑን በመገንዘብ ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅበትን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥምረቱ የሚያከናውናቸው ተግባራት እውን እንዲሆኑ ከጎኑ እንደሚቆምም አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሸማቾች መብት ጥበቃ ማህበራት ጥምረትን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ የተመረጡት አቶ እንግዳ አስፋው የሸማቾች መብት በአዋጅ ላይ ያለ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ግን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ አለመደረጉን ገልጸዋል፡፡
ይህም ሸማቾች ስለመብቶቻቸው በቂ ግንዛቤ ባለመያዛቸውና መብቶቻቸው ሲጣሱም ከለላ የሚሆንላቸው ማህበራት ባለማቋቋማቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዛሬ የተመሰረተው ጥምረት በተለይ ሽማቹን ስለመብቱ ግንዛቤ የመፍጠርና መብቶች ተጥሰው ሲገኙም ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን የህግ ከለላ እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በዛሬው እለት ዓለም አቀፍ የሸማቾች ቀንን “በህብር መብታችንን እናስከብር” በሚል መሪ ሃሳብ አክብሯል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
