





” ሴቶችን እናብቃ! ሰላምን እናስፍን! ልማት እናረጋግጥ!” በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ113ኛ በሀገራችን ለ48 ጊዜ አለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶች ህፃናት ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስተባባሪነት የቴፒ ብዝሃ ማዕከል የክልል ሴክተር መስሪያቤቶች በጋራ አክብረዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወይዘሮ ገነት መኩሪያ እንደገለፁት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማውረስ የሴቶች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የመሪነት ሚናቸውን አጠናክረው ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ሀገር ተረካቢ ብቁ ትውልድ እንዲኖረን ሴቶችን ማብቃት በትኩረት ሊሰራይገባል ያሉት ኃላፊዋ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ አስተዋጽኦ እንዲዳብር በቅንጅት መሰራት አለበት ብለዋል ።
እስካሁን በተካሄዱት ዴሞክራሲያዊና ማህበራዊ የልማታዊ ሥራዎች ሴቶችን ተሳታፊና ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት መኖራቸውን ጠቁመው የሴቶች ካላቸው ሀገራዊ አበርክቶ አንፃር በቂ ባለመሆናቸው በተሳትፏቸው መጠን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥተው መሰራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ለዘመናት ስር ሰዶ የቆየውን በፆታ ላይ የተመሰረተ ባህላዊና ልማዳዊ አድሏዊ አስተሳሰብን በማጥፋት አሁን የተጀመረውን የሰቶችን አመራርነት የማጎልበት ስራ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ወጥ በሆነ መልኩ መተግበር እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
ሴቶች ለሰላም፣ ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እያበረከቱት ያለው አስተዋፅዖ በሀገራችን ከተመዘገቡት ሁለንተናዊ ለውጦች የጎላውን ሚና እንዳላቸው ገልጸው ይህንን ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በእለቱም ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ በክልሉ ሴቶች ህፃናት ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ተደርጓል።
