በአሳታፊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም የአርሶአደሩን ኑሮ ለማሻሻል በተሰራው ስራ አዎንታዊ ውጤት ተመዝግቧል። አቶ ማስረሻ በላቸው

Spread the love

በክልሉ ሁለት ወረዳዎች ሲተገበር የነበረው የአሳታፊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም ምዕራፍ ሁለት በእንግሊዝኛው (PASSDIP-II) መዝጊያ መርሀግብር የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ማስረሻ በላቸውና ለሌሎች የባለድርሻ አካላት በተገኙበት በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።

ፕሮግራሙ ከ7 ዓመታት በፊት በዳውሮ ዞን ሎማ ቦሳ እና ጌና ወረዳ ሁለት ቀበሌያትን በማቀፍ በአነስተኛ የውሃ መስኖ አውታር ግንባታ የአርሶአደሩን ኑሮ በማሻሻል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የኢኮኖሚ አቅምን ለማሳደግ ዓላማ አድርጎ የተነሳ መሆኑ ተገልጿል።

ባለፉት የትግበራ ጊዜያት ፕሮግራሙ በስሩ በታቀፉ ቀበሌያት በአነስተኛ የውሃ መስኖ ግንባታ፣ በግብርና ግብዓት ድጋፍ በአጠቃላይ 200 የሚጠጉ አርሶአደሮችን ተጠቃሚ ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን የተገነቡ የመስኖ አውታሮች ከ180 ሄክታር በላይ ማሳን የሚያለሙ እንደሆነ ተጠቁሟል።

ፕሮግራሙ የአነስተኛ መስኖ ግንባታን መሠረት በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር በአፋርና ውሃ ጥበቃ፣ በእውቀት ሽግግር እንዲሁም ለባለድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት አርሶአደሮችን ከተለመደው የእርሻ ኤክስቴንሽን በማላቀቅ በአመት ሁለት ጊዜና ከዚህ በላይ እንዲያመርቱ ያስቻለ መሆኑን ነው የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ ታመነ ተስፋዬ ያስረዱት።

በአሳታፊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም የአርሶአደሩን ኑሮ ለማሻሻል በተሰራው ስራ አውንታዊ ውጤት መመዝገቡን የገለጹት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ተጠቃሚ አርሶአደሮች በህብረት ስራ ማህበራት በመደራጀት የመስኖ አውታሮች ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ ጥበቃ እንዲያርጉ አሳስበዋል።

አቶ ማስረሻ አክለው በፕሮግራሙ ግንባታው የተጓተተው የቶኒ መስኖ በጀት የተመደበለት በመሆኑ ፕሮግራሙ ቢወጣም ከክልሉ መስኖ ኤጄንሲ ጋር በመቀናጀት ግንባታውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ትኩረት ተደረጎ እየተፋጠነ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

በመድረኩ የተገኙ የባለድርሻ አካላት በበኩላቸው በፕሮግራሙ ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ ስራዎችን በባለቤትነት በማጠናቀቅ ዘላቂ አግልግሎት እንዲሰጥ ተቀናጅተው እንደሚሰሩ እንዲሁም በፕሮግራሙ የተመዘገቡ ለውጦችን ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመዝጊያው መርሃ ግብሩ የፕሮግራሙ ስቲሪንግ ኮሚቴ አባል መስሪያ ቤት የሥራ ሀላፊዎች፣ በፕሮግራሙ የታቀፉ ወረዳ የባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *