በብልጽግና ፓርቲ የህዝባችን የፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያደገ መጥቷል፦ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

H.E Dr.eng Negash Wagesho
Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የክልሉን ሁለት ዓመት ከመንፈቅ የስራ እንቅስቃሴ ከሚዲያዎች ጋር ቆይታ አድርጓል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖለቲካና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን እና የፍትሀዊነት ጥያቄዎችን ተከትሎ የተመሰረተ ክልል መሆኑን ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገልጸዋል ፡፡

ክልሉ የብልጽግና ትሩፋት ሁነኛ መገለጫ ነዉ ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ በብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ሁለት ዓመት ከመንፈቅ በሆኑት ጊዜያቶች በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አብራርተዋል ፡፡

የክልሉን ህዝብ የመልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ደረጃ በደረጃ ምላሽ እየተሰጠ እንደሚገኝም ዶክተር ኢንጀር ነጋሽ ዋጌሾ ተናግረዋል ፡፡

ክልሉ ከተደራጀ ወዲህ የታችኛውን መዋቅር ጥያቄዎች በተለይም የዞን፣የከተማ አስተዳደርና ቀበሌ መዋቅር ጥያቄዎችን በጥናት አስደግፎ ምላሽ እንደተሰጣቸውም ርዕሠ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አብራርተዋል ፡፡

በክልሉ ከለውጡ ማግስት ይታይ የነበረውን የጸጥታ ስጋትና የሰላም መደፍረስ ከህዝቡና ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን አሁን ላይ የተረጋጋ የፖለቲካ አካባቢ በመፍጠር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደቻሉ አብራርተዋል ፡፡

በሸካ ዞን በቴፒና ዙሪያው ፣በቤንች ሸኮ ዞን በሾከና ደቡብ ቤንች ወረዳዎች እና በምዕራብ ኦሞ ዞኖች ይስተዋል የነበረው ይኸው ችግር ተቀርፎ ዜጎች ወደ ልማት ትኩረት ማድረጋቸውንም አብራርተዋል ፡፡

የፖለቲካና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘቱ በክልሉና አካባቢው የሚስተዋሉ የሰላም ችግሮችን በተደራጀ አግባብ ለመፍታትና ልማት ላይ ለማተኮር ዕድል መፍጠሩን አመላክተዋል።

ለዚህም በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመቀናጀት በተሰራው ስራ ክልሉን ሰላም የሰፈነበት ማድረግ መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የተሻለ ተፈጥሮ ሀብት ያለው አካባቢ ያለውና ለግብርና ስራዎች ምቹ ስነ ምህዳር ያለበት በመሆኑ ከዚህ ቀደም የማይታረሱ መሬቶች እንዲታረሱ በማድረግና የበጋ ወቅት ሰብሎችን በማላመድ አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኝም በመግለጫቸው አብራርተዋል ፡፡

በሌማት ትሩፋት ስራዎች ክልሉ የተቀናጀ ስራዎችን በማከናወኑ አሁን ላይ ኢኮኖሚውን የሚያነቃቁ እንዲሁም የስራ ዕድል ፈጠራ ምንጭ በመሆን እየተከናወነ የሚገኝ ተግባር ነውም ብለዋል ፡፡

በክልሉ ከ5 መቶ ሺህ በላይ ሄክታር ቡና ማሳ እንደሚገኝ ያብራሩት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በየዓመቱ ከ60 ሺህ በላይ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ክልሉ ኢኮኖሚ ይበልጥ እንዲያድግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል ፡፡

በክልሉ የሚታየውን የምርት ዘር አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት በሰጠው ቁርጠኛ አመራር የምርጥ ዘር ብዜት ድርጅት በማቋቋም በማምረትና በማዘጋጀት በጅምር ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተገኙ እንደሚገኝም አብራርተዋል ፡፡

የክልሉን ገቢ ከማሳደግ አኳያ በርካታ ስራዎች በሁለት ኣመት ተኩል ውስጥ መሰራታቸውን ያብራሩት ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉ ሲመሰረት 5 ቢሊዮን ብር ዕዳ ይዞ እንደነበር አስታውሰዋል ፡፡

ይህንን ዕዳ በመያዝም ክልሉ ደመወዝ ለመክፈል ይቸገር እንደነበርና ዕዳዎችንም ለመመለስ በተደረገው ጥረት 3.5 ቢሊዮን ብር የመመለስ ስራዎች መከናወናቸውንም እንዲሁ ገልጸዋል ፡፡

ከክልሉ ምስረታ ወዲህ በ2014 ዓ/ም 2.2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ፣በ2015 ዓ/ም 4.2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡንና በ2016 ዓ/ም 6.2 ብር በመሰብሰብ የክልሉን ህዝብ የመልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል ፡፡

በመሰረተ ልማት ዘርፎች በተለይም በመንገድና ድልድይ፣በንጹህ መጠጥ ውሃ ፣በጠየና እና መሰል ጉዳዮች የክልሉ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች መሆናቸውን በመረዳት አቅም በፈቀደ መጠን ህብረተሰቡን በማስተባበርና ከመንግስት በተገኘ ሀብት ውስኖችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተደረገ ይገኛል፤ ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው ብለዋል ፡፡

በክልሉ የህብረተሰቡ ተሳትፎ እጅግ እያደገ መምጣቱን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ከህብረተሰቡ በአይነትና በጥሬ ገንዘብ ከ840 ሚሊየን በላ ብር ማዋጣት ችለዋል ብለዋል ፡፡

በመንገድ፣ በፌደራል ፕሮጀክቶችና መሰል መሰረተ ልማቶች ህብረተሰቡ ለካሳ ክፍያዎች የሚጠበቅባቸውን መዋጮ በማበርከት በክልሉ ልማቶች እንዲፋጠኑ ለማስቻል በሚደረገው ርብርብ የማይተካ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኝም ገልጸዋል ፡፡

ክልሉ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ካለው የተፈጥሮ ጸጋ አኳያ ምቹ መሆኑን ያስረዱት ዶክተር ኢንጀር ነጋሽ ዋጌሾ ታላላቅ ረጂም ዘመናትን ያስቆጠሩ የእምነት ተቋማት፣ ቅርሶች፣ፓርኮች፣ፏፏቴዎችና ወንዞች፣ሐይቆች፣ጥብቅ ደኖች፣የግቤ 3 እና የኮይሻ ሀይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ የሚፈጥረው ሐይቅ፣ሀላላ ኬላ የድንጋይ ካብ እና ሌሎች ተደማምረው ክልሉን የቱሪዝም መዳረሻ ያደርጋሉ ብለዋል ፡፡

ለዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ በክልሉ የዕለት ተዕለት ስራ አድርጎ በመስራት በግብርና ስራ ለተሰማሩ ወጣቶች 37 ትራክተሮችን በመግዛት የመካናይዜሽን እርሻ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገንም እራርተዋል ፡፡

የተቸገሩትን በመርዳትና በመደገፍ ችግሮቻቸውን የመካፈል ልምድ በክልሉ እንዲዳብር ለማስቻል የክልል ቢሮዎች የአረጋውያንን መጠለያ በመስራት ዜጎችን ከወደቁበት ማንሳት ማህበራዊ መስተጋብርን ማጠናከር ስራ ባህል ሆኖ እየተለመደ መምጣቱ ክልሉ መንግሰት ትኩረት ያደረገው ተግባር መሆኑንም አስረድተዋል ፡፡

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *