



የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር እና የሱፐርቪዥን ቡድኑ ሰብሳቢ ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ከሠላምና ፀጥታ አንፃር ክልሉ ሠላም መፈጠሩን እና አጎራባች ክልል እና ህብረተሰቡ ጋር የሠላምና ፀጥታ ትብብር መኖሩ የሚበረታታ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በሠላምና ፀጥታ ዘርፍ የተገኙ ውጤቶች ለማስቀጠል የማህበረሰብ ተኮር የሰላም ግንባታ በማጠናከር የአከባቢ ሠላምና ፀጥታ ጠባቂ እና ባለቤት የማድረግ ስራ እንዲጠናከር አስተያየት ሰጥተዋል።
በክልሉ አረንጓዴ አሻራ ልማት ስራን ውጤታማ ለማድረግ የችግኝ ጣቢያዎችን በማስፋት፣ከሌሎች ክልሎች ጋር ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የችግኝ ስርጭትን ለማድረስ በትብብር መስራት አለበት ብለዋል።
በግብርና ምርትና ምርታማነት የማደበሪያ ስርጭት፣ ኩታ ገጠም የሙዝና የስንዴ ክላስተር እርሻዎች፣ መካናይዜሽን ፣ የበጀት እጥረትን ለማሻሻል የህብረተሰብ ተሳትፎን በማሳደግ የበጀት ጉድለት መሸፈኑ ፣ በክልሉ ምርጥ ዘር መቋቋም እና በእንስሳት መኖ ዝግጅት መልካም ተሞክሮዎች መኖሩን ገልጸው በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡
ክልል ያለውን የመልማት አቅምና ፀጋ የሚመጥን የንቅናቄ ስራዎች መሰራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ክልሉ ባለው አቅሙ መጠን ገቢ ማመንጨ እንዲችል የፖሊሲ እና የህግ ማዕቀፍ ማበጀት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ክልላዊ የምርጥ ዘር ማባዣ ማዕካለትን፣ ለአርሶአደሩ የትራክተር፣ የኮምባይነርና የብድር አቅርቦትንና ስርዓትን በማመቻቸት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቅንጅታዊ ስራን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
ከትምህርት አንፃር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የራስ አቅምን በመጠቀም እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ለሀገር ትልቅ አቅም መሆን የሚችሉ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
በሌማት ትሩፋት እየተሰሩ ያሉ ጅምር ስራዎች አበረታች በመሆናቸዉ ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
በክልሉ በፌደራል መንግስት የተጀመሩ መሰረተ ልማቶች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ ቡድኑ ከሚመለከታቸው የፌዴራል መንግስት አካላት ጋር ይነጋገራል ብለዋል፡፡
ክልሉ ተከታታይ የሆነ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው ያገኘናቸው መልካም አፈጻጸሞቻችንን በመጠቀም ፣ ክፍተቶችን ለመሙላት በቀጣይ የታችኛው የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
ክልሉ ከፍተኛ አቅም ያለዉ ቢሆንም በርካታ የበጀት እጥረትና መሰል ማነቆዎች እንዳሉ የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ ክልላዊ የወጪ መጠንን በመቀነስ በውስጥ ገቢ ለመሸፈን የውስጥ ገቢ አሰባሰብ አቅምን ለማሳደግ በልዩ ሁኔታ ይሰራል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ በከተማ ግብርናና ከወርቅ ማዕድን ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በልዩ ትኩረትና በቅንጅት የሚሰራ መሆኑን ገልጸው ይህ ተግባር እንዲጠናከር በየደረጃው ያለው የክልሉ አመራር በቁርጠኝት ይተጋል ብለዋል።
ድጋፋዊ ሱፐርቪዥን ቡድኑ ጉብኝት ክልሉን በተጨባጭ አቅም የሆነና የሚደግፍ በመሆኑ በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገልጸዋል፡፡
በተከተል ወ/ሚካኤል
