የሴቶችን የአመራርነትና የውሳኔ ሰጪነት አቅም ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል::

Spread the love

የሴቶችን የአመራርነትና የውሳኔ ሰጪነት አቅም ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

በፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት፣ ዩኤን ውሜን እና ቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውዴሽን አስተባባሪነት ከሁሉም የሀገሪቱ አከባቢዎች ለተወጣጡ ሴቶች በስድስት ዙሮች ሲሰጥ የነበረው “የመካከለኛ አመራር ሴቶች ስልጠና” የማጠቃላይ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡

በማጠቃላያ መርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ በከፍተኛ አመራርነት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ጥረቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በስድስት ዙሮች የተሰጠው ስልጠናም የሴቶችን የከፍተኛ አመራርነት አቅም ማሳደግ፣ ወደ መሪነት እንዲመጡ የመደገፍና ማበረታታት ዓላማ ያለው ነው ብለዋል፡፡

ስልጠናው መካከለኛ ሴት አመራሮች የእውቅትና ክህሎት እንዲገነቡና ከአቻ ሴቶች ጋር ልምድ እንዲለዋወጡ ማስቻሉንም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የሴቶችን የአመራርነትና የውሳኔ ሰጪነት አቅም ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ የተሰጠው ስልጠና ተተኪ ሴት አመራሮችን ለማፍራት፣ የአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት አቅማቸውንም ለማሳደግ መሆኑን ገልጸዋል።

በአገር ዕድገት፣ ልማትና ለውጥ ሴቶች ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆኑ በመንግስት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ከማእከላዊ ኢትዮጵያ የመጡት ዙላላ ሁሴን እና ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሐረገወይን ሙራታው፤ ሴቶች በስልጠናው በመሪነት ሚና ጠቃሚ የሆነ ልምድና እውቀት ያገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የተሳተፉት መስከረም ሃይሉ እና ከአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኬሪያ እስማኤል፤ በስልጠናው ጥሩ እውቀት ማግኘታቸውን ጠቅሰው ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀዋል።

በስድስት ዙሮች በተካሄደው ስልጠና ከመንግስት፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ከግሉ ሴክተር የተወጣጡ ከ180 በላይ ሴቶች መሳተፋቸው ታውቋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *