



ሚዛን አማን ፣ መጋቢት 14/2016 በክልሉ ግብርና ቢሮ ለእንስሳት ጤና ባለሙያዎች ሲሰጥ የቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል።
በኢትዮጵያ ከሀገራዊ ጥቅል ምርት የግብርና ዘርፉ 65 በመቶ ያህሉን የሚይዝ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 48 በመቶ የሚጠጋው ደግሞ ከእንስሳት ሀብት ልማት የሚሸፈን መሆኑን ጥናቶች ያመላክታሉ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልም እንደ ክልል አሉ ከሚባሉ ሀብቶች ቀዳሚው የእንስሳት ሀብት ልማቱ ነው። በክልሉ 38 ሚሊየን 550ሺ የሚጠጋ አጠቃላይ የእንስሳት ሀብት ቁጥር እንደሚገኝ በክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊና የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታመነ በቀለ ይናገራሉ።
በክልሉ የሸኮ ጎዳ ከብት ፣ የጫካ ማር ፣ የቦንጋ በግ ዝርያ የመሳሰሉ የእንስሳት ዝርያዎች ይገኛሉ ያሉት ኃላፊው እንደ ሀገር ያለንን የእንስሳት ሀብት ልክ በምርታማነቱ ተጠቃሚ አልሆንም ብለዋል። ለዚህም የዝርያ ፣ የአያያዝና አመለካከት እንዲሁም የእንስሳት ጤና አጠባበቅና የመሳሰሉት ለምርታማነቱ መጓደል እንደ ምክንያት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።
ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን የእንስሳት በሽታዎች በቀላሉ በክትባት ብቻ መከላከል ይቻላል ያሉት አቶ ታመነ በተያዘው በጀት አመት በክልሉ ለ11 ሚሊየን እንስሳት ክትባት ለመስጠት ታቅዶ ባለፉት 7 ወራት 7.5 ሚሊየን ክትባቶች መሰጠታቸውን ገልጸዋል። ቀሪ 3.5 ሚሊየን ክትባቶችን በቀሪ ወራት ለመፈጸም ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
ከቅርብ አመታታ ወዲህ የሌማት ትሩፋት ስራዎች የእንስሳት ልማት ስራው ላይ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩን የገለፁት አቶ ታመነ እንደ ክልል እመርታ ታይቶበታል ብለዋል። በክልሉ በእንስሳት ጤና ዘርፉ የሚታየውን የባለሚያዎች የአመለካከት ፣ የክህሎትና የስነ ምግባር ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል።
በቅርቡ በ6 ዞኖች ፣ በ41 ወረዳዎችና በከተማ አስተዳደሮች በተደረገ የመስክ ምልከታ በተለይም በተዘዋዋሪ የእንስሳት መድኃኒት ፈንድ በርካታ ተግባራት የተፈጸሙ ሲሆን በባለሙያ የታዩ የሙስናና የስነ ምግባር ጉድለቶችን ፈጥኖ ለማረምና በፍጥነት ወደ ስራ ውስጥ ለመግባት ያለሙ መድረኮች እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል ። በቀጣይም እስከታችኛው መዋቅር የኦዲት ስራና እርምጃዎች ይወሰዳሉ ብለዋል።
በመድረኩ የድጋፍና ክትትል ስራዎች ማነስ ፣ የእንስሳት ህክምና ፍቃድ አሰጣጥ ህገ ወጥነት ፣ የተዘዋዋሪ ፈንድ ገንዘቦች ብክነት ፣ የክትባት አፈፃፀም ወጥነት አለመኖርና ዝቅተኛ አፈፃፀም እና በአዲሱ የሰራተኞች የስራ መደብ ጥናትና የደረጃ ዕድገት አፈፃፀም መዘግየት እንደ ችግር ተነስተዋል።
ያነጋገርናቸው የመድረኩ ተሳታፊዎች እንደገለፁት የእንስት ሀብት ልማትና የጤና ዘርፉ ባለፉት አመታት ትኩረት ተነፍጎት የቆየ እንደነበር ገልጸው ከቅርብ አመታት ወዲህ ትኩረት እያገኘና ልማት እየተመዘገበበት መሆነን ገልጸዋል። የእንስሳት ጤና ባለሙያው መድኃኒት በስሙ የሚያወጣ ፣ የሚያክምና ገንዘብ የሚሰበስብ በመሆኑ ለሙስና ተጋላጭ አድርጎታል ብለዋል።
በቅርቡ የአካውንታንት መደብ በመውረዱ መሰል ችግሮች እየተቀረፉና ፈንዱ ለታለመለት አላማ እየዋለ መሆኑን ገልጸዋል ሲል የቤንች ሸኮ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዘግቧል።
