





የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ 62 በመቶ መጠናቀቁን ግንባታውን የሚያከናውነው ሥራ ተቋራጭ አስታወቀ።
የአውሮፕላን ማረፊያውን በተያዘለት ግንባታ ለማጠናቀቅ የአካባቢው የአየር ጸባይ ፈተና መሆኑን ተቋራጩ ገልጿል።
የሳምሶን ቸርነት ስራ ተቋራጭ ስራ አስኪያጅ እንጂነር ኢዮብ ሞላ በሥፍራው ለሚገኙት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢዎች እንደገለጹት፣ የአውሮፕላን ማርፊያው በ930 ሚሊዮን ብር በጀት እየተገነባ ነው።
የአውሮፕላን ማረፊያው ከፍተኛ የህዝብ የልማት ጥያቄ ያለበት በመሆኑ በልዩ ትኩረት እየተገነባ ነው። በተለይ የዞኑ አስተዳደር የወሰን ማስከበር ስራ በቅርበት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ገለጻ የአውሮፕላን ማረፊያው ደረጃውን የጠበቀ ትልልቅ በረራዎችን ማስተናገድ በሚያስችል መልኩ እየተገነባ መሆኑን ጠቅሰዌ።
አጠቃላይ ርዝመቱ 2 ነጥብ 8 ኪሎሜትር የሚሸፍን የመንደርደሪያ ስፍራ ያለው ይህ ፕሮጀክት፤ ከዚህ ውስጥ እስካሁን ባለው በወሰን ማስከበር የተነሳው 2 ነጥብ 4 ኪሎሜትር ሲሆን ቀሪው 400 ሜትር የወሰን ማስከበር ስራውን የዞኑ አስተዳደር እየሰራ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
እስካሁን ባለው የግንባታ አፈጻጸም በዋናነት የአፈር ድልደላ ስራ መሰራቱን የጠቆሙት ኢንጂነሩ፣ ቦታው ለግንባታ ረግረጋማ በመሆኑ አስቸጋሪ ቢሆንም ይህን በመቋቋም ግንባታው የቀጠለ ሲሆን የቀጣዩ ምእራፍ ግንባታ መጀመሩንም ገልጸዋል።
ለግንባታው ሙሉ ግብአት መዘጋጀቱን የጠቆሙት ኢጂነር ኢዮብ በቀጣይ አመት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ኢፕድ ዘግቧል።
የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የግንባታ መሰረት ድንጋይ መቀመጡ ይታወሳል።
