




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት በክልሉ ክላስተር ከተሞች ደረጃቸውን የጠበቁ ባለ ዘጠኝ ወለል ህንጻዎችን ለማስገንባት በተዘጋጀው ዲዛይን ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መከረ።
የክልሉ መንግሥት በክላስተር ከተሞቹ ለሚስገነቧቸው ህንጻዎች የዲዛይን ስራውን በኢትዮጵያ ግንባታና ዲዛይን ስራዎች ኮርፖሬሽን ማሰራት ተገልጿል።
የግንባታ ዲዛይንና ቁጥጥር ስራው አዲስ በተቋቋመው የመንግስት የልማት ድርጅት በሆነው የደቡብ ምዕራብ ዲዛይን ግንባታ ቁጥጥር ኮርፖሬሽን እና በአጋርነት በሚሰራው የኦሮሚያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን እንደሚደረግ ተብራርቷል።
በቀጣዮቹ ቅርብ ቀናት የዲዛይን ማሻሻያዎችን በማካተት የጨረታ ዶክመንት ተዘጋጀው ወደ ግንባታ ግዥ መገባት እንዳለበት ያሳሰቡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበጀት ዓመቱ ማገባደጃ የግንባታ ስራውን በይፋ ለማስጀመር ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በግንባታና ዲዛይን እንዲሁም የኮንትራት አስተዳደር ያለውን የካበተ ልምድ ለክልሉ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ኮርፖሬሽን እንደሚያጋራው የተገለፀ ሲሆን በተዘጋጀው ዲዛይን ላይም ግምግማ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል።
ኮርፖሬሽኑ የዲዛይን ግምገማውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ የማሻሻያ ሀሳቦችን እንዲያቀርብ የተጠየቀ ሲሆን የክልሉ መንግሥት እስካሁን የተከናወኑ ዝርዝር ተግባራት አቅርበዋል።
በተዘጋጀው የህንጻው ዲዛይን ላይ የባለድርሻ አካላት ሙያዊ ሀሳብ አስተያየት ሰጥተዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
