የጠቅላይ ሚኒስትሩ “ጽዱ አካባቢ ለሀገር ግንባታ” ኢኒሼቲቭ ምንድን ነው::

Spread the love

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ እየሠሯቸው ካሉት ሥራዎች መካከል ጽዱ ቢሮን፣ ጽዱ ከተማን እና ጽዱ ሀገርን መፍጠር አንዱ ነው፡፡

“ከቢሮ፣ ግቢ፣ ሠፈር እስከ ሀገር” ብለው ከጽ/ቤታቸው የጀመሩት ይህን እንቅስቃሴ ከአዲስ አበባ አልፎ ወደ ተለያዩ የክልል ከተሞች እያደገ ሀገር አቀፍ ሆኗል፡፡

ሰው አካባቢው ጽዱ ከሆነ መልካም ነገርን የማሰብን ኃይል ያገኛል የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለዚህ ደግሞ መንግሥት ተቋማቱን ጽዱ በማድረግ ምሳሌ መሆን የጀመረውን ሥራ ወደ ከተማ እና ሌሎች ተቋማት አሳድጎ ምሳሌነቱን አሳይቷል፡፡

የግል ተቋማትም ይህንኑ አርአያነት እየተከተሉ የመሥሪያ ቦታዎቻቸውን ውብ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጽ/ቤታቸውን የኢትዮጵያን ምስል በሚመጥን መልኩ ካደሱ በኋላ “ገበታ ለሀገር” በሚል እንቅስቃሴ አንድነት ፓርክን፣ ወዳጅነት አደባባይን እና እንጦጦ ፓርክን ውብ አድርገው ሠርተዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጎርጎራ፣ ወንጪ እና ኮይሻ በገበታ ለሀገር ተሠርተው የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል የሆነው የሸራተን ሆቴል ጎዳናም እነዚህን ፕሮጀክቶች የተሟሉ በሚያደርግበት መልክ ተሠርቶ አካባቢውን ውብ አድርጎታል፡፡ አዲስ አበባ በሁሉም ረገድ በዚህ ደረጃ የፀዳች እና ለነዋሪዎቿ የተመቸች፣ የእንግዶቿን ቆይታ የምታሳምር እንድትሆን እየተሠራ ነው፡፡

ዕይታችንን አስፍተን ትልማችንን ከፍ አድርገን ከሠራን ሀገራችን ያሏትን ሀብት ተጠቅመን ማደግ እና ለትውልድ የምትሆን ውብ ሀገር መሥራት እንደምንችል በተግባራዊ እንቅስቃሴ እያሳዩ ይገኛሉ፡፡

ሌላው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው ሀገራዊ ፕሮጀክት የጫካ ፕሮጀክት ነው፡፡ የጫካ ፕሮጀክት አካባቢው የተፈጥሮ አረንጓዴነቱን ሳያጣ ለሰው ልጆች መኖሪያ እና መዝናኛ እንዲሆን ታልሞ እየተሠራ ያለ ትልቅ ፕሮጀክት ነው፡፡

እነዚህ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን በሥርዓቱ ተጠቅማ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ እያደረጓት እንዲሁም እያለን ያልተጠቀምንባቸውን ሐብቶቻችንን እንድናይ እያደረጉን ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራችን ያላትን ገጽታ በማሳመር የቱሪስት መስሕብ እየሆኑም ነው፡፡

ይህ ከቢሮ ተነስቶ እስከ ሀገር የደረሰውን ጽዱ እና አረንጓዴ አካባቢን የመፍጠር ፕሮጀክት በ”ገበታ ለትውልድ” ደግሞ በስምንት ክልሎች መስራት ተጀምሯል፡፡

ከእነዚህም መካከል በትግራይ ክልል ገራ አልታ፣ በኦሮሚያ ክልል ጅማ፣ በአማራ ክልል ሐይቅ፣ በደቡብ ክልል አርባ ምንጭ፣ በአፋር እና ሱማሌ ክልሎች መሠራት የጀመሩት ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፕሮጀክቱ እንዲሳካ ካላቸው ፍላጎት የተነሳም “የመደመር ትውልድ” የተሰኘ መጽሐፋቸውን ሙሉ ገቢ ለዚህ ፕሮጀክት አበርክተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለእነዚህ ፕሮጀክቶች መነሻ ያደረጉት የኢትዮጵያን ትልቅነት የሚመጥን ሥራ መሥራት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ያልተነኩ እና አቧራ የለበሱ ሐብቶች እንዳሏት የሚጠቅሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ እነዚህን ሐብቶቻችንን አቧራቸውን አራግፈን ለእይታ ካበቃን ኢትዮጵያን ዳግም እንድትወለድ እናደርጋለን ይላሉ፡፡

ይህን ሥራ ሙሉ ለማድረግም የዲፕሎማሲ መዲና የሆነችው ከተማችን ደረጃዋን እና ስሟን የሚመጥን ንጽህና ሊኖራት እንደሚገባ ታምኖ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

ሰዎች በየመንገድ ዳሩ ከመጸዳዳት ወጥተው ንጽህናውን በጠበቀ ቦታ የመጸዳዳት ባህላቸውን እንዲያሳድጉ፣ ለዚህ ደግሞ ደረጃቸውን የጠበቁ መጸዳጃዎች እንዲሠሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢኒሼቲቭ ወስደው እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

ይህን ኢኒሼቲቭ ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት ሰዎች አካባቢያቸውን በንጽህና እንዲጠብቁ ከማድረግ ጎን ለጎንም ክብራቸውን ጠብቀው እንዲጸዳዱ በየአካባቢው መጸዳጃ ቤቶች መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል፡፡

የመጸዳጃ ቦታዎቹ ከተዘጋጁ በኋላ የአጠቃቀም ሕጉ እንደሚዘጋጅም አስታውቀዋል፤ ይህ ኢንሼቲቭ ከተማችንን ምቹ እና ለጤና ተስማሚ እንድትሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ኢኒሼትቩን ሁሉም ተቋማት እና ግለሰቦች እየተቀላቀሉት ሲሆን፣ በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታትም ሥራዎቹ ተጠናቀው ለህዝብ ይፋ እንደሚደረጉም ይጠበቃል፡፡

የዲፒሎማሲ ማዕከል እና የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ለብዙ ዘመናት ያልታደሰች ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የቆሻሻ አወጋገዷ በጣም ኋላ ቀር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አሁን እየተሠራ ካለው የኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞም ሰዎች ንጽህናውን በጠበቀ አካባቢ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ አካባቢውን የሚመጥን የቆሻሻ ማስወገጃዎች እና መጸዳጃ ቤቶች መሠራታቸው ምንም የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡

ይህን እውን ለማድረግም ህብረተሰቡ ተባብሮ መሥራት እንዳለበት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳሰቡት፡፡

ዘገባው የኢቢሲ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *