በ11 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የቦባ ቆጫ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታው ተጠናቅቆ ተመረቀ።

Spread the love

ትምህርቤቱ በኢፌዴሪ ገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉሙሩክ ኮሚሽን በጋራ መገንባቱ ተገልጿል ።

በክልሉ ካፋ ዞን ዋቻ ከተማ የተገነባው የቦባ ቆጫ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾና የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታና የጉምሩክ ኮሚሽን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተመርቋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ባስተላለፉት መልዕክትም የትምህርት ተቋማት መሠረታዊ ችግሮች መጠነ ሰፊ በመሆናቸው ችግሮችን ለመፍታት ደረጃ በደረጃ በመስራት ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በዚህም ባለሃብቱ፣መንግስትና ህብረተሰቡ በመቀናጀትና በመተባበር ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሚገኙም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል ።

በክልሉ ሁለንተናዊ ለውጦችን ለማስመዝገብ የብልጽግና አስተሳሰቦችን በሁሉም መስክ ማረጋገጥ አለብን ብለዋል።

በቦባ ቆጫ ተገንብቶ በተጠናቀቀው ትምህርት ቤት ድጋፍ ያደረጉ የኢፌዴሪ ገቢዎች ሚኒስቴርንና የጉሙሩክ ኮሚሽንን በክልሉ መንግስት ስም አመስግነዋል ።

የኢፌዴሪ ገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስት ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ቱሉ የዋቻ ከተማ አስተዳደር በተሰጠው ሀብት በታማኝነት ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት አስገንብቶ ለምረቃት በማብቃቱ በተቋማቱ ስም አመስግነዋል ።

የኢፌዴሪ ገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝና ለትምህርት ቤቱ አይሲቲ አገልግሎት የሚውል 20 ላፕቶፕ እና ዴስክ ቶፕ ድጋፍ አድርገዋል ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በበኩላቸው በክልሉ ከ85 ከመቶ በላይ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በክልሉ ከደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በማድረግ በርካታ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን ተናግረዋል ።

የፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉሙሩክ ኮሚሽን በክልሉ ካፋ ዞን ቦባ ቆጫ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስገንብቶ ለምረቃ ማብቃቱ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል ።

በክልሉ በተደረገው ንቅናቄም ከ414 ሚሊዮን በላይ ብር ተሰብስቦ የተለያዩ የትምህርት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም አቶ አልማው ተናግረዋል ።

በተገነባው ትምህርት ቤት ወላጆች ልጆቻቸውን ተከታትለው ማስተማር እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

የካፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ንጉሴ ባስተላለፉት መልዕክት በቦባ ቆጫ የተገነባው ትምህርት ቤት የነገውን ትውልድ ህይወት የሚቀይር መሆኑን ተናግረዋል ።

በቦባ ቆጫ የተገነባው ይህ ትምህርት ቤት የዞኑን የትምህርት ስብራት የሚቀይር ነውም ብለዋል።

በዕለቱም በትምህርት ቤት ምረቃ ላይ የተገኙት የአካባቢው ተወላጆችና ግንባር ቀደም ግብር ከፋይ የሆኑት አቶ ወንድሙ ወ/ሚካኤል እና አቶ መንግስቱ መንገሻ ለትምህርት ቤቱ ቁሳቁስ ማሟሟያ እያንዳንዳቸው የ100 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል ።

አቶ መንግስቱ መንገሻ ከቦባ ቆጫ ትምህርት ቤት ድጋፍ ባለፈም በተማሩባቸው የጨና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንድ ብሎክ ትምህርት ቤት ለመገንባት ቃል ገብተዋል።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *