




የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚና ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በቦንጋ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን በተሰሩ ጥናቶች ላይ ተጨማሪ ግብዓት የማሰባሰብ አውደ ጥናት ዛሬ አጠናቋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ በቋንቋዎችና በባህሎች ላይ ከአዲስ አበባ፣ ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲትና ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ታርጫ ካምፓስ ምሁራን የተሰሩ 19 የጥናትና ምርምር ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን ከተሳታፊዎችም ጥናቱን ውጤታማ የሚያደርጉ ተጨማሪ ግብዓቶች የተገኙበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአውደ ጥናቱ ማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ ጥናት ያደረጉ አካላት ችግሮችን ተቋቁመው መስራታቸውን አድንቀው ቀጣይ ክልሉ እያገዘ የተጀመሩ ስራዎች እንደሚጠናቀቁ ቃል ገብተዋል፡፡
የክልሉ ምክትል አፈ-ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፀሐይ ዳርጫ በበኩላቸው ምሁራኑ ለፍተውና ደክመው የሰሩት የጥናትና ምርምር ስራዎች ተጠናቀው ተግባሪዊ እንዲሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ማገዝ አለባቸው ብለዋል፡፡
የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ በበኩላቸው ቅንጅታዊ አሰራሮችን በመዘርጋት ለጥናትና ምርምር ሥራዎች ተግባራዊነት ክልሉ የድርሻውን ይወጣል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም በአቶ ፍቃዱ ወ/ማሪያም የተጻፈና በክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የታተመው “የናኦ ህዝብ ኢትኖ-ሂስትሪ” (Ethno-history) የተሰኘ መጽሃፍ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የአውደጥናቱ ተሳታፊዎች በተገኙበት ለካፋ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ርክብክብ ተደርጎ መድረኩ ተጠናቋል፡፡
በውቢት ደበበ
