




የሆስፒታሉን ተግባር አፈጻጸም የሚገመግም የቦርድ አባላት የጋራ ውይይት ተካሂዷል።
የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ዳዊት ገበየሁ በውይይቱ ላይ እንዳሉት ሆሲፒታሉ አገልግሎቱን እንዲያሳልጥ የሚያግዝ ድጋፍ በተገቢ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ሆስፒታሉ ከሚሰጠው የአገልግሎት ስፋትና ከግብአት አቅርቦት አኳያ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት እየተሰራ እንደሚገኝም ዋና አስተዳዳሪው አስገንዝበዋል።
የ9 ወራት የሥራ ሪፖርት ያቀረቡት የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ያዕቆብ ሌንጫ እንዳብራሩት የሆስፒታሉን አገልግሎት በሰለጠኑ ባለሙያዎች የታገዘ ለማድረግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
የሆስፒታሉ አገልግሎት ተደራሽነት ከዞኑ ወጪ ያሉ አካባቢዎችን ጭምር የሚሸፍን ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ የውስጥ አሰራሮችን የማስተካከልና ተዛማጅ ሥራዎችን የመከታተል ተግባራት ላይ ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።
የሆስፒታሉን አቅም ለማሳደግ ሀብት የማፈላለግ ስራዎችን በመስራት በክልሉ መንግስት ድጋፍ ከሚገነባው ህንፃዎች በተጨማሪ በኢት ማዕድን አክሲዮን ማህበር በተገኘ 2.4 ሚሊዮን ብር የፋርማሲ ህንጻ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ብለዋል።
አያይዘውም በሆስፒታሉ በተወሰኑ የሥራ ክፍሎች የሚታየውን የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ በቀጣይ ከቦርዱ ጋር በመሆን ለማሟላት እንደሚሰራም አስገንዝበዋል።
የዳውሮ ዞን የጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አስራት ቸርነት በበኩላቸው በሆስፒታሉ ባሉ የጤና ባለሙያዎች አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ርብርብ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተቋሙ እንደችግር የተነሱት ጉዳዮችን በቀጣይነት ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች ባቀረቡት አስተያየትና ጥያቄዎች ዙሪያ ውይይት ተደርጎ ከመግባባት ላይ ተደርሷል።
በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የተመራው የቦርድ አባላት የሆስፒታሉን የሥራ እንቅስቃሴና በሂደት ላይ ያሉ ግንባታዎችን ጎብኝተዋል።
