




በቤንች ሸኮ ዞን የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ገለፀ።
በዘንድሮው አመት ለመጀመሪያ ጊዜ በሚዛን ቴፒ ዩንቨርሲቲ እየተሰጠ ያለውን ኦንላይን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ የሙከራ ፈተና አሰጣጥ ሂደት የዩኒቨርስቲው የዞንና የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር አመራሮች በተገኙበት ጉብኝት ተካሂዷል።
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ግሩም ተማም እንደተናገሩት በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ በ4 ትምህርት ቤቶች የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ የሚሰጥ ሲሆን ከዚህ ቀደም የሚያጋጥሙ የውጤት መቀነስን ለማስቀረት የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘንድሮው አመት ለመጀመሪያ ጊዜ በኦንላይን በሚሰጠው አገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና በከተማ አስተዳደሩ የሚገኘው የዕድገት ትምህርት ቤት መመረጡን ተናግረው ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከሚዛን ቴፒ ዩንቨርስቲ ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የዞኑ ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ አገኘሁ ወርቁ እንደገለፁት በዞኑ በዘንድሮው አመት ከ5ሺህ 100 በላይ ተማሪዎች መልቀቂያ ፈተናውን እንደሚወስዱ ተናግረዋል።
በተለይ ዘንድሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ኦንላይን የሚሰጠውን መልቀቂያ ፈተናውን እንደዞን በተሳካ መልኩ ለማከናወንና ውጤት ለማምጣት የሚዛን ቴፒ ዩንቨርሲቲ ለተማሪዎች እያደረገ ያለው ድጋፍና እገዛ ከፍተኛ በመሆኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የሚዛን ቴፒ ዩንቨርስቲ የምርመራና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ግርማ ጥላሁን በበኩላቸው ዩንቨርስቲው ከመማር ማስተማር ስራው ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ ጥቅም የሚሰጡ በርካታ አገልግሎቶች መስራት ተቀዳሚ ተግባሩ ነው ብለዋል።
በዚህም በዞኑ በዘንድሮው አመት ለመጀመሪያ ጊዜ በዩንቨርሲቲው ኦንላየን ለሚሰጠው 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን ለማብቃት በቂ የሙከራ ፈተና በማዘጋጀት እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል።
የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ስንታየሁ ጋይድ በበኩላቸው በኦንላይን የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ሃገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር በበቂ ሁኔታ ልምምድ እያደረጉ መሆናቸውንና በቀጣይም ተማሪዎችን የማብቃት ስራ በቅንጅት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
