





በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ አዘጋጅነት በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አፈፃፀምና በወባ ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ የክልሉ ምክር ቤት አባላት በተገኙበት በቦንጋ ተካሂዷል።
በምክክር መደረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ መድረኩ የአስፈጻሚ አካላት አፈፃፀምን በመገምገም የህዝብ ውክልናን በአግባቡ ከመወጣትም በላይ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ በሚታዩ ችግሮች ለይቶ አስፈፃሚ አካላትን ለማገዝ እንደሚረዳ አንስተዋል።
አክለውም የአስፈጻሚ አካላትን አፈጻጸም በየጊዜ መገምገም የምክር ቤትና የአስፈጻሚ አካላት ተቀራርቦ በመስራት የህዝብ ቅረታዎችን ለመፍታት ምቹ መደላደልን እንደምፈጥር ጨምሮ አንስተዋል።
የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እተሻሻለ እንደሆነ በማንሳት የሚፈለገውን ደረጃ እንዲደርስ ለማድረግና የህዝብን እርካታ ለማሳደግ የም/ቤቱ አባላት ገምጋሚና ጠያቂ ብቻ ሳይሆን በመቀራረብ ድጋፍና ክትትልና እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባ የተከበሩ አፌ ጉባኤው በአጽንኦት አንስተዋል።
የክልሉ ም/ቤት ምክትል አፌ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፀሐይ ዳርጫ በበኩላቸው ይህ መድረክ በክልል ደረጃ የተፈጠረው የንቅናቄ መድረክ በተገቢው ወደ ታች ስለመውረድን ለመፈተሽና ከጤና ጣቢያ እስከ ሆስፒታል ያለው ትስስር በማጠናከር እና የማህበረሰብ ጤና አገልግሎት በማሻሻል የዘርፉ ተግባር ወጤታማ ለማድረግና ወረርሽኙን ለመግታት ወሳኝ ሚና እንዳለው አሳስበዋል።
በምክክር መደረኩ ላይ የተሳተፉት የም/ቤቱ አባልና የመንግስ ረዳት ተጠሪ የተከበሩ አቶ በላይ ተሰማ የጤና ጉዳይ የተቋሙና የም/ቤት አባላት ብቻ ባለመሆኑ የመንግስት አካላትና ሁሉም አደረጃጀቶችን በማሳተፍ የወባ ወረርሽኙ ልንከላከል ይገባል ብለዋል ።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ምክር ቤቱ ከተቋሙ ጋር በርካታ ተግባራትን በማገዝ እየሠራ መሆኑን አስታውሰው የመድኃኒት አቅርቦት እንዲሻሻል፣ በጀት በማስመደብ፣በአገልግሎት አሰጣጥ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ፣ የማህበረሰብ ጤና አገልግሎት እንዲሻሻል በማድረግ ውጤት እንዲመጣ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አንስተዋል ።
በመሆኑም የጤና ኤክስተንሽን ባለሙያዎችን ከማሟላት አንጻር በተቋሙ አበራታች ስራ እየተሰራ የቆየ መሆኑን በማንሳት የጤና ኤክስተንሽን ፕሮግራሙ የንቅናቄው አፈፃፀም የደረሰበት እንዲሁም የወባ ወረርሽኝ በአሁኑ ጊዜ በተቋሙ ላይ ጫና ከመፍጠሩም በላይ ለህዝባችን ደህንነት ስጋት እየሆነ በመምጣቱ የም/ቤቱ አባላት በጥልቀት በመገምገም በመከላከልና መቆጣጠር ረገድ ለማገዝና የጋራ መፍትሔ አቅጣጫ ላይ የሚያተኩር የምክክር መድረክ እንደሆነ ጠቁመዋል ።
በመድረኩ ላይ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አፈፃፀምና በወባ ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ላይ ያተኮረ ሰነድ ለተሳታፊዎች በዶ/ር እንዳሌ ሳህሌ ቀርቦ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የወባ ወረርሽኝ በሁሉም ተቋማት የጋራ አጀንዳ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል ።
በቀረበዉ ሰነድ ላይ የም/ቤቱ አባላት ውይይት ያካሄዱት ሲሆን የክልሉ ጤና ቢሮ እና የም/ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች እስከ ቀበሌ ወርዶ መደገፋቸው ፣ ቢሮው በአሁኑ ሰዓት አሰጊ የሆነ ወረርሽኙን በጥልቀት በመገምገም የጋራ መፍትሔ ለማምጣት መድረክ ማዘጋጀቱ፣ በተቋማት የመድኃኒት አቅርቦትና አገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ መምጣቱ እና አገልግሎትን በማሻሻል የህዝብ ቅረታ ለመፍታት የተጀመሩ ተግባራት በጥንካሬ ተገምግሟል ።
በተቃራኒው የወባ ወረርሽኝን አመራሩ ለይቶ ስትራተጂክ ሆኖ ከመደገፍ አንጻር ውስንነት መታየቱ፣ የታችኛው ም/ቤቶች የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ክትትልና ቁጥጥር ማነስ፣ የመድኃኒት አቅርቦትና ስርጭት ላይ አልፎ አልፎ ህገ ወጥነት መታየት ፣ በየደረጃው ያሉ የጤና ቦርድ ያለመጠናከር፣ የሴቶች ልማት ህብረት አለመጠናከር ፣የእናቶች ማቆያ ችግር የአጎበር ስርጭትና ተደራሽነት እና የባለድርሻ አካላት ቅንጅት በሚፈለገው ልክ አለመሆን ከዘርፋ ተግባር ስፋትና ከወረርሽኙ አንገብጋቢነት አንጻር ትኩረት እንደሚሻ ተመልክቷል ።
በምክክር መድረኩ ላይ የክልሉ ም/ቤት አባላትና ቋሚ ኮሚቴዎች፣ የዞን አፈ ጉባኤዎች፣ የጤና ቢሮ ም/ኃለፊዎችና የማኔጅመንት አባላት የተገኙ ሲሆን ተሳታፊዎቹ በግምገማው የተነሱ ጠንካራ አፈፃፀም ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በጉድለት በተነሱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠትና የባለድርሻ አካላት በቅንጅት መረባረብ እንደሚገባ አቅጣጫ በማስቀመጥ መድረኩ ተጠናቋል ።
በጌታሁን ግርማ
