“ቢስት ባር” የቤንች ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል የዓለም ዓቀፍ የባህል ሀብት ሊሆን በሚችል መልኩ ባህላዊ ዕሴቱንና ይዘቱን በጠበቀ አኳኋን ለማክበር እየተሰራ መሆኑን የቤንች ሸኮ ዞን ባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ::

Spread the love

የብሔረሰቦች በዓላት እንደ ብሔረሰቡ ማንነት፤ አሰፋፈር፣ ባህላዊ የዘመን አቆጣጠርና ወቅቶችን መሰረት በማድረግ በጋራ በመሰብሰብ ያከብራሉ፡፡
በዚህም ወቅቱን የሚዋጅና እርስ በእርስ የሚያስተሳስራቸውን የጋራ አጀንዳ ይቀርፃሉ፤ ይነጋገሩበታል፤ ይወቃቀሱበታል ያለፈውን የአሁንና የወደፊቱ ታሪካቸው ዙሪያ ይወያያሉ፤ ይከራከራሉ፤ ያርማሉ፤ ያደራጃሉ፤ ያለማሉ ለቀጣዩም ትውልድ ያሸጋግራሉ፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት 13 ነባር ብሔር፣ ብሔረሰቦች ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር ተዋደው፣ ተዛምደውና ተጋምደው በሠላምና በመከባበር ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ የቤንች ብሔረሰብ ነው።
የቤንች ብሔረሰብ ካሉት በርካታ ከሚዳሰሱና ከማይዳሰሱ ታርካዊና ባህላዊ ቅርሶችና ትዉፊቶች መካከል አንዱ የብሔረሰቡ የዘመን መለወጫ ”ቢስት ባር” በዓል ነው፡፡
በዓሉ ከረጅም አመታት በፊት በቀደምት አያቶቻችንና በአባቶቻችን ባህላዊ ይዘቱንና ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተከበረ የቆየና በመሀል ተቋርጦ የነበረ እንጂ አዲስ የተፈጠረ እንዳልሆነ የቤንች ሸኮ ዞን ባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ኮይካ ገልፀዋል፡፡
በዓሉ ከማንኛውም ባህላዊ እምነትም ሆነ ዘመናዊ ኃይማኖትና የአምልኮ ሥርዓት ጋር ምንም ግኑኝነት የሌለው የብሔረሰቡ የዘመን መለወጫ በዓል ሲሆን ለበዓሉ ከሌሎች በዓላት በተለየ የረዥም ወቅት ዝግጅት እንደሚደረግለትም ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
አቶ ጌታቸው አክለው “ቢስት ባር” የቤንች ብሔር ዘመን መለወጫ በዓልን የዓለም ዓቀፍና የሀገር የባህል ሀብት ሊሆን በሚችል መልኩ ባህላዊ ዕሴቱንና ይዘቱን በጠበቀ አኳኋን ለማክበር የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ እንዳሉትም ገልጸዋል።
የቤንች ብሔረሰብ የራሱ ታሪክና ማንነት መነሻ አለውና ይህን ታሪክና እውነታን መሰረት በማድረግ የዘመን መለወጫ በዓል የመከበሪያ ቦታ ያለው መሆኑን የገለፁት አቶ ጌታቸው ይህም የብሔረሰቡ ታሪካዊ መገኛ በሆነው ዣዥ እና በአማን አየር ሜዳ በብሔረሰቡ ታሪክ ውስጥ ሁልጊዜ የቀደምት አባቶቻችን ታታሪነትና ስራ ወዳድነትን ለሚመጣው ትውልድ የሚያስተላልፈው ሜዳ ላይ በተለያዩ ኩነቶች እንደሚከበርም አንስተዋል።

ባህላዊ በዓላት በመደበኛ እና አልፎ አልፎም በአንዳንድ ምክንያቶች መነሻ በወካይ ቀናቶች የሚከበሩ ሲሆን የቤንች ብሔረሰብ የራሱን ዘመን መለወጫ በዓል ከህዳር መጨረሻ እስከ ታህሳስ መግቢያ ባሉት በመደበኛ ቀናት ሲያከበር የራሱ የሆነው ምክንያት ያለው መሆኑን የገለፁት ኃላፊው እንደ መከበሪያ ቦታ ሁሉ ባህላዊ ክብረ በዓላት አከባበር ቀን የራሱ የሆነ ባህላዊ ምክንያትን ታሳቢ በማድረግ ይወሰናል ብለው ቀኑ በማህበረሰቡ ውስጥ የራሱ የሆነ የታሪክ ትውስታ ሊኖረው ስለሚችል ለአብነት የደስታ፣ የምስጋና፣ የጥጋብና ሌሎች ታሪካዊና ሃይማኖታዊ እንዲሁም ባህላዊ ይዘትን ታሳቢ በማድረግ ቀኑ ሊመረጥ ይችላል ብለዋል፡፡
ወቅቱ እህል የሚደርስበት ስለሆነ ማህበረሰቡ መጀመሪያ የደረሰውን እህል የሚቀምስበት ወቅት በመሆኑ የበረከትና የጥጋብ፣ ያለው ለሌለው የሚለግስበት፣ ክረምት የነበረው ጭጋግ ጨለማው አልፎ በጋ ሲወጣ በብርሃን የሚተካበት፣ በአደይ አበባዎች አከባቢው የሚከበብበት ከመሆኑም ባሻገርም በዓሉ ዓመታዊ ከመሆኑም ጋር ተያይዞ ህዝቡ ሰላሙና ጤናው ተጠብቆ በሰላምና በአንድነት የሚያከብር በዓል ስለሆነ ”የምስጋና” በዓልም ጭምር ነው ሲሉ አቶ ጌታቸው አብራርተዋል።
በታርካዊም ሆነ በባህላዊ መንገድ በማህበረሰቡ ዘንድ ለበዓሉ ትልቅ ትርጉምና ቦታ ይሰጣል ያሉት የመምሪያው ኃላፊ ”ቢስት ባር” በዓል ከረጅም ዓመታት በፊት በቀደምት አያቶቻችንና አባቶቻችን ዘመን ባህላዊ ይዘቱንና ትውፊቱን ጠብቆ እየተከበረ የነበረ መሆኑን አመላክተዋል።
ይህም ቀደም ሲል በተወሰኑ አከባቢዎችና በተወሰኑ ኩነቶች ብቻ ሲከበር የነበረውን በዓል የአሁኑ ትውልድ እንደማህበረሰብ ሰብሰብ ባለ መልኩ ባህላዊ ይዘቱንና ትውፊቱን አስጠብቀው በዘመነ መንገድ በዓሉ ለዓለምና ለሀገር የባህል ሀብት ሆኖ እንዲያገለግል ጭምር በተደራጀ መንገድ እየሰራ እንዳለና ለበዓሉም አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶችን እያከናወነ እንደሚገኝም አንስተዋል።
እንደማህበረሰብ የአሁኑ ትውልድ ከባህል፣ ከወግ፣ ከቋንቋና ከማንነት ጋር ያለው ቁርኝነት እንዲሁም ታናናሾች ለታላላቆች የሚሰጡት ክብር እጅጉን እየቀነሰ የመጣ በመሆኑ ክብረ በዓሉ በቀድሞ አያቶቻችንና አባቶቻችን ዘመን የነበረውን ትልቁን የብሔረሰብ የመከባበር፣ የመቻቻል፣ የመተሳሰብና የመታዘዝ ባህልዊ ዕሴት መመለስ በሚችል መልኩ ይከበራል ብለዋል አቶ ጌታቸው።
ትውልዱም የራሱን ባህል፣ ቋንቋና ማንነት በትክክል አውቀው፣ ተገንዝበውና አክብረው ለቀጣይ ትውልድ እንዲያሸጋግር በትውልዱ ላይ ይሰራልም ያሉት አቶ ጌታቸው የዘንድሮው የቤንች ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ ቢስት ባር በዓል ለማክበር በአከባቢውና ከአከባቢው ዉጭ ያሉ የአከባቢው ተወላጆችና የሚመለከታቸው የማህበረሰብ አካላት ተጀራጅተው በዓሉን ለማክበር ኮሚቴ ተቋቁሞ ማህበረሰቡም በመሳተፍ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በቁርጠኝነት እየተሳተፈ ይገኛል ብለዋል።
የዘንድሮ የቤንች ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል ከግንቦት መጨረሻ እስከ ሰኔ መግቢያ ድረስ የሚከበር ሲሆን የመከበሪያ ቦታ የብሔረሰቡ ታሪካዊ መገኛ በሆነው ዣዥ እና በአማን አየር ሜዳ ላይ በተለያዩ ኩነቶች ማጠቃለያ እንደሚከበርም ተናግረዋል፡፡
በዓሉ የብሔረሰቡ ክብርና የማንነት መገለጫ እንደመሆኑ መጠን ሁሉም የሚመለከተው አካል ኮሚቴ ውስጥም ሆነ ከኮሚቴ ውጪ ያለ ሁሉ ለበዓሉ ስኬት የራሱን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበው በድጋሚ “ለቢስት ባር” በዓል እንኳን በሰላምና በጤና አደረሳችሁ ብለዋል።


ኢትዮጵያ በርካታ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መገኛ ናት። ብሔረሰቦች የራሳቸውን ማንነት የሚገልጹ ቀለማት፣ የዘመን አቆጣጠር፣ ቋንቋ፣ የባህል አልባሳት፣ የዘመን መለወጫ በዓላትና ሌሎች አያሌ የማንነት መገለጫዎች አሏቸው ።
እንደሀገርም ሆነ እንደክልል እነዚህ አያሌ የብሔረሰቦች ታርክ፣ ባህልና ወግ ይዘቱን አስጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማሸጋገር ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ያሉ ሲሆን በዚህም አሁን ያለው ትውልድ የበኩሉን ሚና መወጣት ይገባል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *