የምስራቅ አፍሪካ አገራት የባለብዙ ወገን ትብብራቸውን በማጠናከር ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት በጋራ ሊሰሩ ይገባል

Spread the love

የምስራቅ አፍሪካ አገራት የባለብዙ ወገን ትብብራቸውን በማጠናከር ለቀጣናው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች ገለጹ።

በምስራቅ አፍሪካ የሚስተዋለው የኃይል ፉክክር በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ፈተና እየሆነ መምጣቱንም አመላክተዋል።

ምስራቅ አፍሪካ የአውሮፓ መካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ የሚተሳሰሩበት ስትራቴጂካዊ ቀጣና ሲሆን፤ የዓለም ፖለቲካዊ ምጣኔ ኃብታዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ መዘውር እንደሆነ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር ካላት መልክዓ-ምድራዊና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር አኳያ የቀጣናው ቀውስ ለብሔራዊ ጥቅሟ ቀጥተኛ አንድምታ እንዳለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጹ ይታወቃል።

በመሆኑም የቀጣናው ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ ከአጋር አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እንደምትሰራ አመልክቷል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ተመራማሪ መሐመድ ሰይድ(ዶ/ር)፤ በመካከለኛው ምስራቅ የሚከሰቱ ችግሮች በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና ጸጥታ ላይ ተጽዕኖው ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ።

በምስራቅ አፍሪካ የሚስተዋለው የኃይል ፉክክር ደግሞ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ፈተና መሆኑን ጠቅሰው፤ አገራት የባለብዙ ወገን ትብብራቸውን በማጠናከር ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት በቀይ ባህር የንግድ እንቅስቃሴ ላይ እየፈጠረ ያለው መስተጓጎል በአፍሪካና በቀጣናው ምጣኔ ኃብት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩንም ገልፀዋል።

በኢንስቲትዩቱ የአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ዳይሬክቶሬት ተመራማሪ ሚፍታህ መሐመድ በበኩላቸው፤ መካከለኛው ምስራቅና ምስራቅ አፍሪካ ታሪካዊ ግንኙነትና መልክዓ-ምድራዊ ቀረቤታ ያላቸው መሆኑን አብራርተዋል።

ከዚህም አንጻር በመካከለኛው ምስራቅ የሚከሰት ችግርና ውጥረት በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አለመሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም የምስራቅ አፍሪካ አገራት በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ የትብብር አማራጭን ሊጠቀሙ እንደሚገባ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) በቀጣናው ካለው አቅም አንጻር የመካከለኛው ምስራቅ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ከሌሎች ቀጣናዊ ተቋማት ጋር በትብብር መሥራትና ጉዳዩን በተመለከቱ የዲፕሎማሲ ምክክሮች ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበትም አንስተዋል።

የኢጋድን የቀይ ባህር ግብረ-ኃይል በአዲስ መልክ በማንቀሳቀስ የቀጣናውን ጥቅምና ፍላጎት ማስጠበቅ ይገባል ብለዋል።

የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይ በቀይ ባህር የንግድ መስመር ላይ የፈጠረው መስተጓጎል በኢትዮጵያ ላይ ጫና የሚያሳድር በመሆኑ የወደብ አማራጮችን ማስፋትም ተገቢ መሆኑን ጠቅሰዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *