


በኢፌዴሪ ግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የተውጣጡ የኢንስፔክሽን ቡድን በካፋ ዞን ጊንቦ እና ዴቻ ወረዳዎች ምልከታ አድርገዋል።
የኢንስፔክሽን ቡድኑ በዞኑ ተዘዋውሮ በተመለከተባቸው ወረዳዎች የቀረቡ የግብርና ግብኣት አቅርቦት ስርጭት ለበልግ የእርሻ ወቅት በተገቢው ስርጭት መካሄዱን መመልከታቸዉን የቡድኑ አስተባባሪ ወ/ሮ አልማዝ ወዳጆ ተናግረዋል ።
በአንዳንድ ቀበሌዎች የሚታየው የመንገድ መበላሸት ከወቅቱ የዝናብ ሁኔታ ጋር ተግዳሮት እንዳይሆን ከወዲሁ ሊታሰብበት እንደሚገባ አመላክተዋል።
በቀረቡት የግብርና ግብኣቶች በየአካባቢው የሚታየው የበልግ እርሻ ቡቃያዎች በተሻለ ቁመና ላይ መሆናቸው በመኸሩም እርሻ ተጠናክሮ ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።
በጊንቦ ወረዳ ሾምባ ሼካ ቀበሌ በአንድነት ክላስተር የለማው የበቆሎ ሰብል የሚበረታታ መሆኑንም ተናግረዋል ።
በኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር ዴስክ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር መለሰ በራኔ በሰጡት አስተያየት የግብርና ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ በወቅቱ የአፈር ማዳበሪያዎች ስርጭት መደረጉን ተናግረዋል ።
በክልሉ ተዘዋውረው በተመለከቱት የአፈር ማዳበሪያ ወደ አርሶ አደሩ በወቅቱ ቀርበው ጥቅም ላይ መዋላቸው የሚበረታታ ነው ሲሉ ተናግረዋል ።
የአፈር ማዳበሪያን ለአርሶ አደሩ ከማድረስ አኳያ አልፎ አልፎ የሚታዩ የመጋዘን እጥረትና የመንገድ መበላሸት ህብረተሰቡ ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል ።
ወ/ሮ ሹርቤ ገመዱ በበኩላቸው በበልግ እርሻ አርሶ አደሩ በተሻለ መልኩ የአፈር ማዳበሪያን መጠቀሙን የሚያመላክቱ ስራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል ።
የሾምባ ሼካ ቀበሌ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ መስፍን መንገሻ ለቡድኑ በሰጠቱት ገለጻ በቀበሌው 547.5 ሄክታር በበቆሎ ሰብል ለመሸፈን በማቀድ 399 ሄክታር በዘር ተሸፍኗል ብለዋል ።
ከዚህም ውስጥ የኢንስፔስክሽን ቡድኑ በተመለከተው በአንድነት ክላስተር ብቻ 38 ሄክታር መሬት በበቆሎ የተሟላ ግብኣት በመጠቀም መልማቱን ተናግረዋል ።
የቀበሌው አርሶ አደር አሸብር አስፋው በበልግ የግብርና እርሻ ከዚህ በፊት የነበረውን ችግር ቀርፎ ዘንድሮ በወቅቱ በማግኘታችን የተሻለ ምርት ለማግኘት ሰርተናል ብለዋል።
ለመኸር እርሻውም በሌሎች ሰብሎች ለመሳተፍ ከወዲሁ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አማካሪና የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ መላኩ በሰጡት አስተያየት በኢፌዲሪ ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በክልሉ ሁለት ዞኖች የግብርና ግብኣት አቅርቦት፣ስርጭትና ክምችትን ለመመልከት በመጡበት ወቅት ያለውን አፈጻጸም በጥሩ ሁኔታ መመልከት መቻላቸውን ተናግረዋል ።
በክልሉ የአፈር ማዳበሪያ ከመኸር ወደ በልግ ያደረውን ጨምሮ 217 ሺህ ኩንታል ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
እስካሁን ባለው መረጃ የ2016/17 የእርሻ ወቅት 132 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከጅቡቲ መቅረቡንና ከመኸር ወደ በልግ የተሸጋገረ 58 ሺህ ኩንታል በድምሩ 190 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ቀርቦ እየተሰራጨ ይገኛል ብለዋል።
ይህም በወቅቱ በመድረሱ አርሶአደሮች በወቅቱ በመጠቀም በበልግ እርሻ የተሻለ ስርጭት መከናወኑን አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል ።
የኢንስፔክሽን ቡድኑ ተመልክቶ የሰጠው አስተያየት ለመኸር እርሻ ወቅት የተጠናከረ ስራ ለመስራት አቅም የሚሆን ነውም ብለዋል።
በታጠቅ አበበ
