የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም አርሶ አደሩ በአካባቢው የሚገኙ የልማት አቅሞችን በተሻለ ሁኔታ እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ::

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በዳውሮ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ተዟዙረው የሌማት ትሩፋት ውጤቶችን ምልከታ አድርገዋል።

ህብረተሰቡ የምግብ ዋስትናውን በማረጋገጥ ትርፍ አምራች እንዲሆን በመንግስት የተለያዩ ፕሮግራሞች ተነድፈው በየደረጃው ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል።

ከእነዚህም ፕሮግራሞች አንዱ በጠቅላይ ሚነስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ተጠቃሽ ሲሆን ዘርፉ የምግብ ዋስትንን ከማረጋገጥ ባለፈ የሀብት ምንጭ ሆኗል።

በዞኑ ኢሠራ ወረዳ በፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦች የተሻሻለ ዝሪያ ያሏቸው ላሞች በማርባት በኑሯቸው ተጨባጭ ለውጦች ማስመዝገብ መቻላቸውን አብራርተዋል።

የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም በአካባቢያቸው የሚገኙ ተፈጥሮ ሀብቶችን አቀናጅተው በትብብር እንዲጠቀሙ ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረላቸውም ተናግረዋል።

ውጤቱን ይበልጥ ለማስፋፋት የሚያግዙ ዝሪያ ማሻሻያ ግብአቶችንና ተከታታይ ድጋፎችን መንግስት አጠናክሮ እንዲቀጥል አርሶ አደሮቹ ጠይቀዋል።

ተዘዋውረው በጎበኙበት ወረዳዎች የተመለከቷቸው የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ተስፋ ሰጪ የሆኑ ጅምሮች የተመዘገቡ መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገልጸዋል።

አርሶ አደሮች በአካባቢያቸው ያለውን እምቅ ሀብትና ጉልበት እንዲሁም ጊዜያቸውን አቀናጅተው እንዲጠቀሙ የሌማት ትሩፋት ሥራው ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረላቸው መመልከታቸውንም አስረድተዋል።

ብልጽግናን ለማረጋገጥ በየደረጃው እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ መሪዎችና ህብረተሰቡ በትብብር መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል።

በዞኑ ከተለያዪ አካባቢዎች የሚቀርቡ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት መንግስት አቅም የፈቀደውን ሁሉ እንደሚያደርግ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ በሁሉም ዘርፎች የህብረተሰቡ ትብብርና ተሳትፎ ሊጎለብት እንደሚገባ ከህዝብ ጋር ባካሄዱት የጋራ ወይይት ላይ ማሰባሰባቸዉን የዞኑ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዘግቧል።

በዞኑ ቶጫ፣ ከጪ እና ኢሳራ ወረዳዎች በተደረገው የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ጉብኝት ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የክልሉ እና የዞን የሥራ ኃላፊዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራንና እንግዶች የተሳተፉ ሲሆን የተለያዪ ችግኞችን በመትከል የአረንጓዴ አሻራ አኑረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *