ይህ የምክር ምዕራፍ በቀጣዩ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ምክክር የሚደረገባቸውን መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ለመለየቱ ስራ ቁልፍ ሚና አለው – መስፍን አርዓያ(ፕ/ር)

Spread the love

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የከተማ አስተዳደርና ክልላዊ የምክክር ምዕራፍ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምሯል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ÷ ኮሚሽኑ በምሁራን ፣ልሂቃንና በተለያዩ የፖለቲካ ተቋማት ጥያቄ የመንግስት ፈቃድና ፍላጎት ታክሎበት በ11 ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች በሚገባ ተቃኝቶ መቋቋሙን አውስተዋል፡፡

የተደራጁ የሃይማኖት፣ የሲቪል ማህበረሰብ እና የፖለቲካ ተቋምትን በየደረጃው በማካተት በ4 ምዕራፍ በከፋፈላቸው የሥራ መርሐ ግብሮቹ ውስጥ ሁለቱን በማጠናቀቅ ወደ ሶስተኛው መርሐ ግብር ማለትም የምክክር ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

በዚህ የምክክር ሒደት ተሳታፊ የሚሆኑት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሃሳብ እና የፖለቲካ መሪዎች እንዲሆኑ በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ በግልፅ መደንገጉንም ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ እነዚህን መሰረታዊ ሃሳቦች መነሻ በማድረግ ተሳታፊዎችን የመለየት ስራውን አሳታፊና አካታች በሆነ መንገድ ለማከናውን አስፈላጊ የሆኑ ተግባራትን በጥንቃቄ ሲያከናውን መቆየቱን ገልፀዋል፡፡

በዚህ መልኩ የተለዩ ተወካዮች በሒደቱ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ከሚያደርጉባቸው ምዕራፎች መካከል ዋነኛ የሆነውን የምክክር አጀንዳዎችን የመለየት ሒደት ዛሬ በይፋ እንደሚጀመርም አስታውቀዋል፡፡

“ይህ የምክክር ምዕራፍ ነው የምንልበት ምክንያት በቀጣይ በሚካሄደው ሀገራዊ ጉባዔ ምክክር የሚደረገባቸውን እጅግ መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች አሳታፊና አካታች በሆነ ሂደት የመለየቱ ስራ በራሱ ምክክር የሚፈልግና መግባባትን የሚጠይቅ በመሆኑ ነው፡፡ ” ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ከመዲናዋ 119 ወረዳዎች የተወጣጡ ተሳታፊዎች ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች የሚወክሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *