ፋና ወጊ ትሩፋት!ወ/ሮ ሞሚና መሀመድ ፋና ወጊ በሆነ ስራዎቻቸው ለ25 ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠርም የሌሎች ኢትዮጵያዊያንን የኢኮኖሚ ችግር በመቅረፍና ተጠቃሚ በማድረግ የድርሻቸውን በመወጣት ላይ ናቸው።

Spread the love


በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በህዳር 6/2015 ዓ.ም የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በተገኙበት የአንድ ቀን መነሻ ፖቴንሻል ምልከታና የአንድ ቀን ዉይይት በማካሄድ ክልላዊ የሌማት ትሩፋት ይፋዊ ስራ ማስጀመሪያ ፕሮግራም በማድረግ ወደ ስራ መገባቱ ይታወቃል።
በሌማት ስራዎች ወደ ተግባር ከተገባ በአንድ ዓመት ውስጥ በርካታ ለውጦች በክልሉ እየተገኙ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመላክታል።
የሌማት ትሩፋት ዓላማ በ2015 ጅምር አመት የተመዘገቡ ስኬቶችን በማጎልበት እና ጉድለቶችን በማረም በሀገራዊ የሌማት ትሩፋት የ4 ዓመት መርሃግብር የተቀመጡ ዝርዝር ዓላማና ግቦች ማሳካት ነዉ፡፡
በዚህም የወተት፣ የዶሮ ስጋና እንቁላል እንዲሁም የማር ምርቶችንና በተጨማሪ የዓሳና ስጋ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በሚሰሩ ስራዎች የላም ወተት በ2015 ከተደረሰበት 316.668 ሊትር በ2016 ወደ 352.73 ሚሊዮን ሊትር ለማድረስ የንቅናቄ ስራዎች ተሰርተው ወደ ተግባር ተገብቷል ።
ምግብና ስርዓት ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የዉጪ ንግድ ገቢ ማሳደግ ከዉጪ የሚገባ ምርት በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የስራ እድል ፈጠራን ማሳደግ ደግሞ በዘርፉ የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው።
ይህንን የሌማት ትሩፋት ንቅናቄን ተከትሎም በክልሉ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ እና ውጤቶችም እየተገኙ ነው። ከሌማት ትሩፋት ስራዎች ውስጥ አንዱ በወተት ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለው የስራ እንቅስቃሴ በክልሉ 6 ዞኖች እየጨመረ መጥቷል።
ከ6ቱ ዞኖች አንዷ በሆነችሁ ቤንች ሸኮ ዞን በወተት ላሞች ርባታ የሚሳተፉ አርቢዎች ቁጥር ከፍ እያለም መምጣት ጀምሯል። በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ኩጃ ቀበሌ ውስጥ አንዲት እናት የወተት ላሞችን በማርባት ከዘርፉም ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል ።
እኚህ ታታሪ ስማቸው ወ/ሮ ሞሚና ጀማል ይባላል ። ለስራ ጉዳይ በአረብ ሀገር በቆዩበት ወቅት በወተት ላሞች መበልጸግ እንደሚቻል በቆዩባቸው ዓመታት ልምድ በመቅሰም ለምን? በሀገሬ ይህንን ስራ አልሰራም? በማለት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል ።
ወ/ሮ ሞሚና ጀማል በሰው ሀገር ለፍተው ጥረው ግረው ባገኙት ወረት ወደ አካባቢያቸው በመመለስ በቤተሰብ ይዞታ ላይ ፋና ወጊ ስራቸውን ከጀመሩ ስድስት ወራትን አስቆጥረዋል ።
የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸውን 3 የወተት ላሞችን ለማርባት ዕቅድ በመያዝ አካባቢው ካለው ምቹነት የተነሳ ዕቅዳቸውን ከፍ በማድረግ 11 የወተት ላሞችን በመግዛት ዛሬ ላይ 3 ጥጆችን በማግኘት ቁጥራቸውን 14 ማድረስ መቻላቸውን አስረድተዋል ።
በዚሁ በሚኖሩበት ኩጃ ቀበሌና ቢፍቱ ከተማ ያለውን የወተት አቅርቦት ዕጥረት ለመቅረፍና በኢኮኖሚው ተጠቃሚ ለመሆን በሌማት ትሩፋት የወተት ላሞች ፋና ወጊ ስራዎችን በማቀድ በተሰማሩበት ስራ በቀን 130 ሊትር ወተት በማቅረብ በተገኘው ሀብት ኑሯቸውን እየመሩ እንደሚገኙም አስረድተዋል።
ከሚያረቧቸው የወተት ላሞች ዝቅተኛ 8 ሊትር ወተት እንዲሁም ከፍተኛው 46 ሊትር ወተት በቀን ከአንድ ላም እንደሚያገኙም ወ/ሮ ሞሚና ተናግረዋል ፡፡
ወ/ሮ ሞሚና ሴትነት ሳይበግራቸው በጀመሩት የወተት ላሞች ርባታ ባለመታጠር የዶሮ ርባታ፣የበግና ፍየል ማሞከት እንዲሁም በንብ ማነብ ለመሰማራት ዕቅድ ይዘው እየሰሩ ይገኛልም።
በዕቅዳቸውም 11 ጊደሮችን በተጨማሪነት ለማስገባት፣ አሁን ባላቸው 15 ቀፎዎች ላይ ተጨማሪ 85 ቀፎችን የማስገባት፣ እንዲሁም ሌሎች የሌማት ስራዎችን አስፍቶ ለመስራትም ራዕይ መሰነቃቸውን አብራርተዋል ፡፡

በአረብ ሀገር ስራ ፍለጋ ሄደው ለሚቸገሩ ኢትዮጵያዊያን በሀገር ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል እኔ ማሳያ ነኝ በማለትም ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው ሐበልጸግ እንደሚገባቸው ምክራቸውን ለግሰዋል።
አሁን ባሉበት የቤተሰብ ይዞታ በተሰማሩበት የሌማት ትሩፋት ስራዎች ካለው የቦታ ጥበት የተነሳ ስራቸው እንዳይስተጓጎል መንግስት ተጨማሪ ማስፋፊያ ቦታ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።
የወ/ሮ ሞሚና ጀማልን የሴት ልጅ ፋና ወጊ ስራ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በወተት ላሞች ርባታ ስፍራ በመገኘት ስራዎቻቸውን ተመልክተዋል።
ወ/ሮ ሞሚና በሰሯቸው ፋና ወጊ ስራዎች መደሰታቸውንና መንግስትም ከልማቱ ጎን ሆኖ እንደሚያግዛቸው አበረታትተዋቸዋል።
የክልሉ መንግስት በ2016 ዓ/ም በወተት ምርት ለመድረስ ያለመውን ዕቅድ ለማሳካትም የወ/ሮ ሞሚና ፋና ወጊ ስራ አንዱ ማረጋገጫ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *