የሲንጋፖር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

Spread the love

የሲንጋፖር ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል በመጠቀም በኢትዮጵያ በግብርና እና ሌሎች ዘርፎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሲንጋፖር ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሲንጋፖር አቻቸው ቪቪያን ብላከሪሽናን (ዶ/ር) ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው እንዲሁም የጋራ ትብብርን በሚጠይቁ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

ሁለቱ የስራ ሃላፊዎች በተለይ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም ቀጣይነት ያለው የልማት ትብብሮች ዙሪያ ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት አስታውቀዋል።

አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ሲንጋፖር በአለም አቀፍ ደረጃ የፋይናንስ፣ ዲጂታል ኢኮኖሚ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ማዕከል በመሆን ያላትን ስትራቴጂካዊ ስፍራ አድንቀዋል።

በዚህም የሲንጋፖር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ስማርት ከተማ ልማትና ስማርት ግብርናን በማስፋት፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ በቱሪዝም አገልግሎትና በትምህርት ዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።

የሲንጋፖር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪቪያን ብላክሪሽናን (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ሲንጋፖር በአፍሪካ በተለይ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት ተሳትፎዋን ማጠናከር እንደምትፈልግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢን ለመፍጠር እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው፤ በሀገራቱ መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ፊት ያለውን መልካም እድል መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *