









ዓለም በግሎባላይዜሽን አማካኝነት ወደ አንድ መንደር በመቀየሯ ምክንያት የተፈጠሩ ዕድሎችን በተገቢው ለመጠቀም እና ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ሀገራችን ልማታዊ ባለሀብቶችን ከየትኛዉም የዓለማችን ክፍል በመሳብ ያልተጠቀምንባቸው ሀብቶች በተገቢው ለምተው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የምንችልበትን የኢኮኖሚና ቴክኖሎጂ አቅም ለመፍጠር ፖሊሲ ከማውጣት ጀምሮ በርካታ ተግባራትን እየፈፀመች ትገኛለች፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተነደፈውን ፖሊሲና ስትራቴጂ በመተግበር የህዝቡን ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ እንደየ ሥራ ፀባያቸው የተለያዩ ተቋማትን አደራጅቷል፡፡ በዚህ መልክ ከተዋቀሩት ተቋማት መካከል የንግድና ኢንቨሰትመንት ቢሮ አንዱ ነው፡፡
ቢሮው የኢንቨስትመንት ስራውን ለማሳካት በሀገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ የወጡ የልማት ፖሊሲዎችን፣ ደንቦችን፣ መመሪያዎችን፣ ፕሮግራሞችንና የተለያዩ አሰራሮችን በተገቢው በመረዳት፣ ለልማት አጋሮች እና ለህበረተሰቡ ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በማከናውን በሁሉም አከባቢ መነቃቃትን በመፍጠር ተደራሽ ለማድረግና ለማመጣጠን የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከበደ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡
ከክልሉ ምስረታ በፊት የኢንቨስትመንት ፍሰት ነባራዊ ሁኔታን በተመለከተም ከ20 ዓመት በፊት በተወሰኑ ኢንቨስተሮች በክልሉ በጥቂት ዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች እንደተጀመረ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ከበደ ተስፋዬ እንደሚገለፁት በቤንች ሸኮ ዞን በግብርና ኢንቨስትመንት ፍሰት 106 ፕሮጀክቶች 44 ሺህ 779.195 ሄክታር መሬት በመረከብ በቡናና ቅመማቅመም፣ በዓመታዊ ሰብል፣ በተቀናጀ ግብርና፣ በጎማ ዛፍ ልማት፣ በእንስሳት ድለባና በማር ልማት እየለማ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
በምዕራብ ኦሞ ዞን በግብርና ኢንቨስትመንት ፍሰት በቡናና ቅመማ ቅመም፣ በዓመታዊ ሰብል፣ በተቀናጀ ግብርና፣ በፍራፍሬ ልማት በ64 ፕሮጀክቶች 38 ሺህ 443 ሄክታር መሬት እየለማ ይገኛልም ብለዋል፡፡
በኮንታ ዞን የግብርና ኢንቨስትመንት ፍሰትም ቡናና ቅመማ ቅመም፣ ዓመታዊ ሰብል፣ በተቀናጀ ግብርና 18 ፕሮጀክቶች በ5 ሺህ 630 ሄክታር መሬት ላይ እየለሙ እንደሚገኙ አቶ ከበደ ገልጸዋል፡፡
በዳውሮ ዞን በግብርና ኢንቨስትመንት ፍሰት ቡናና ቅመማ ቅመም፣ በዓመታዊ ሰብል፣ በተቀናጀ ግብርና፣ እንስሳት ድለባ፣ በደን ልማት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ 33 ፕሮጀክቶች በ5 ሺህ 411.5 ሄክታር መሬት ላይ እየለሙ መሆኑንም እንዲሁ አብራርተዋል፡፡
በሸካ ዞን በግብርና ኢንቨስትመንት ፍሰት ቡናና ቅመማ ቅመም፣ ዓመታዊ ሰብል፣ ሻይ ልማት 46 ፕሮጀክቶች 17 ሺህ 751.442 ሄክታር መሬት እየለማ ሲሆን በካፋ ዞን በግብርና ኢንቨስትመንት ፍሰት ቡናና ቅመማ ቅመም፣ ዓመታዊ ሰብል፣ ሻይ ልማት ፣እንስሳት ድለባና ማር ልማት 159 ንዑስ ፕሮጀክቶች 28 ሺህ 082.832 ሄክታር መሬት በመረከብ ወደ ልማት መግባታቸውን አስታውሰዋል ፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተመሰረተ ወዲህ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት የፍሰት ለውጥ መኖሩንም ኃላፊው አመላክተዋል፡፡
ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ለሁሉም ዞኖች ያላቸዉን ፖቴንሻል/ሀብት/ ማለትም ቡና፣ አመታዊ ሰብሎች፣ ፍራፍሬ፣ ወርቅ፣ የብረት ማዕድ፣ የድንጋይ ከሰል የመሳሰሉትን በክልሉ የተመጣጠነ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲኖር ለማስቻል ከፍተኛ የማስተዋወቅ ስራ በመሰራቱ ፍሰቱ ሊጨምር ችሏል ብለዋል፡፡
ክልሉ ከተመሰረተ በኋላ ተወስነው ወደ ስራ የገቡ ፕሮጀክቶች ግብርና 127፣ አገልግሎት 42፣ ኢንዱስትሪ 13 በጠቅላላ 182 ፕሮጀክቶች ወደ ስራ መግባታቸውን ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
እንደ ክልል አጠቃላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ብዛት በክፍለ ኢኮኖሚ ሲታዩ በግብርናው 426 ፕሮጀክቶች፣ በኢንዱስትሪ 312 ፕሮጀክቶችና በአገልግሎት 91 ፕሮጀክቶች በድምሩ 829 ፕሮጀክቶች በስራ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
ኢንቨስተሮች ወደ ክልላችን አንዲመጡ የክልሉ መንግስት ባደረገዉ ጥሪ የአካባቢ ተወላጅ ዲያስፖራዎች ወደ ክልላችን በመምጣት በዳዉሮ፣ ካፋ፣ ምዕራብ ኦሞ እና ቤንች ሸኮ ዞኖች ኢንቨስት ማድረግ መጀመራቸውንም አቶ ከበደ አብራርተዋል፡፡
በዚህም 16 ቢሊዮን 069 ሚሊዮን 042 ሺህ 483 ብር ካፒታል ተመዝግቧል፤ ለ1 ሺህ 563 ቋሚ የሥራ ዕድል ለዜጎች ተፈጥሯል ፣ለ5 ሺህ 962 የአካባቢዉ ኅ/ሰብ የአስተራረስ ዘዴ፣ የተሻሻሉ ዝርያዎችን መጠቀም፣ የማዳበሪያ አጠቃቀም፤ የቡና ዘርና ምርት አዘገጃጀት፣ የሻይ ልማት ስራ፣ የመስኖ አጠቃቀም እና በመሳሰሉት የቴክኖሎጂና የዕዉቀት ሽግግር ተደርጓል፡፡
የክልሉ መንግስት አልሚ ባለሀብቱ በክልሉ ኢንቨስት ማድረግ በሚችልባቸው አማራጮች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማሟላት ለመቀበል ዝግጁ መሆኑንም በዚሁ አጋጣሚ ጥሪ አድርጓል፡፡
አጠቃላይ የኢንቨስትመንት አፈጻጸምን በተመለከተ መሬት ከተረከቡ 409 የግብርና ፕሮጀክቶች 139 ሺህ 068.89 ሄክታር መሬት ተላልፎ 70 ሺህ 023.99 ሄክታር መሬት መልማት መቻሉን የቢሮው የ9 ወራት የስራ አፈጻጸም መረጃ ያመለክታል፡፡
በታጠቅ አበበ
