




በካሜሮን ዱዋላ ከተማ በሚደረገው 23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለሚካፈለው የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን በዛሬው ዕለት ሽኝት ተደረገለት።
በ23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከተዘጋጁት 45 የሜዳ ላይ ተግባራት ኢትዮጵያ በ41ዱ ትሳተፋለች።
በሻምዮናው ኢትዮጵያ በ34 ሴት እና በ43 ወንድ በድምሩ በ77 አትሌቶች ትሳተፋለች።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዘዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በሽኝት መርሃ ግብሩ፤ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንደ ኦሊምፒክ ላሉ ውድድሮች መነሻ ነው ብለዋል።
ይሄ ዓመት ውድድሮች የበዙበት ፈታኝ ዓመት ነው ያሉት ፕሬዘዳንቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አትሌቶችን ለማብቃት ላደረገው ጥረት ሊመሰገን ይገባል ነው ያሉት።
የእያንዳንዱ አትሌት ምኞት ውጤት ማምጣትና ኦሊምፒክ ላይ መሳተፍ በመሆኑ እንደ አፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያሉት ውድድሮች ትልቅ መነሻ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ፤ አትሌቶች በቆዩበት የ15 ቀናት የልምምድ ጊዜ እርስ በእርስ ለመተዋወቅ ረድቷቸዋል ብላለች።
የልዑክ ቡድኑ ከነገ በስትያ ረቡዕ ጠዋት 3 ሰዓት ላይ ወደ ካሜሮን ዱዋላ ከተማ እንደሚጓዝ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
