
የከተማ ትልቁ ሀብት መሬት ነው።የከተሞች ውስን ሀብት የሆነው የከተማ መሬትን በአግባቡ ማስተዳደር ከተማን የሚመጥን ፕላን ማዘጋጀት ያስፈልጋል።
የከተማ ፕላን የአንድን ከተማ እና የአካባቢውን የወደፊት ዕድገት የህዝቡን ጥቅም እና የከተሞችን እድገት መሰረት በማድረግ እንዲመራ ተደረጎ የሚዘጋጅ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ ሲሆን በይዘት ደረጃ የከተማውን መሬት አጠቃቀም፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ታሪካዊ፣ የፊዚካላዊና ሌሎች ጉዳዮችን ያካትታል፡፡
ከተሞች በፕላን ሲመሩ ለከተማው ህብረተሰብ ኑሮና ለሥራ ምቹ አካባቢ ይፈጥራል፤ ውስን የከተማ መሬት በአግባቡ ለመጠቀም ይረዳል፤ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ለመደልደልና ተደራሽ ለማድረግ ከማገዝ ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እና የመልካም አስተዳደር ጉዳይን በአግባቡ ለመፍታት ያስችላል፡፡
የአገራችን ከተሞች በፕላን እንዲመሩ ማድረግ ከተጀመረ ቆየት ያለ ቢሆንም አሁንም የከተሞች ፕላን ዝግጅትም ሆነ አተገባበር የሚፈለገው ደረጃ ላይ ያልደረሰ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በክልላችን የሚገኙ ከተሞች ልማታቸውን በፕላን እንዲመሩ በማድረግ ሰፋፊ ከተሞች በዙሪያቸው የሚገኙ የገጠር ማዕከላትና ሌሎች ከተሞች ጋር ተሳስረው ማድግ እንዲችሉ እንዲሁም ከደረጃቸው ጋር የሚመጥን የተለያዩ የፕላን አይነቶችን በማዘጋጀት የትግበራ ሁኔታቸውን በመከታተል ረገድ በርካታ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ኃይሌ በክልሉ ከስድስቱ ዞኖች 10 ከተሞችን ለፈርጅ አምስት ብቃታቸውን በመመዘን ከነበሩበት ከገጠር ማዕከልነት ወደ ከተማነት ማሳደግ እንደተቻለም ተናግረዋል።
በዚህም ክልሉ ከተመሰረተ በሁለት ዓመት ውስጥ የክልሉ ከተሞች ቁጥር ቀደም ሲል ከነበረበት ከ96 ወደ 106 ማደግ ችሏል ነው ያሉት።
በእነዚህ በተለያየ ደረጃ ለሚገኙ ከተሞች የተለያዩ ደረጃ እና ዓይነት ያላቸው 86 የሚሆኑ ፕላኖች መዘጋጀታቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
አቶ ፀጋዬ አክለውም የከተማነት ባህሪ ላላቸው፣ የገበያ ማዕከል የሆኑ፣ በተነጻጻሪም አቀማመጣቸው ለከተማ ማዕከልነት ተመራጭነት ላላቸው 45 የገጠር አገልግሎት ማዕከላት የስኬች ፕላን(sketch plan) ማዘጋጀት ችለናል ነው ያሉት።
እነዚህም ከተሞች ገና ሲመሰረቱ በፕላን የመመራት ልምድ እንዲኖራቸውና ማዕከላቱ ወደ ከተማ ሲያድጉ መሰረታዊ ፕላን ለማዘጋጀት እንዲቻል መሰረት ለመጣል እንደሆነም አቶ ፀጋዬ ጠቅሰዋል።
ለ37 ከተሞችም የመሰረታዊ ፕላን(Basic plan) ማዘጋጀት ተችሏል ያሉ ሲሆን ይህም ለፈርጅ አራት እና ለፈርጅ አምስት ከተሞች የሚዘጋጅ የፕላን አይነት መሆኑንም አስረድተዋል።
በያዝነው አመት ከሃያ ሺህ በላይ የከተማ ነዋሪ ላላቸው ከተሞችም በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን የደብረወርቅ ከተማን ጨምሮ ዋካ፣ ቢፍቱ፣ አመያ፣ ጪዳ እና ደካ ከተሞች ስትራቴጂክ ፕላን (Strategic plan) እንደተዘጋጀና ይህንንም ፕላን ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችሉ የሰፈር ልማት ፕላኖች በተለያየ ደረጃ መሰራታቸውን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አንስተዋል።
ከተሞችን መልሶ ከማደስና ከመለወጥ አኳያ በቦንጋ ከተማ 43 ሄክታር የከተማ ቦታ የሚሸፍን የሰፈር ልማት በማዘጋጀት ወደ ትግበራ መገባቱን ለአብነት የጠቀሱት አቶ ፀጋዬ ኃይሌ ከዚህ ልምድ በመውሰድ በአመያ እና ጪዳ ከተሞች ሰፈር ልማት ፕላን ከማዘጋጀት ጎን ለጎን የከተማ ዲዛይን(Urban design) ስራ ተሠርቷል ብለዋል።
እንደ አቶ ፀጋዬ ኃይሌ ገለጻ ተዘጋጅቶ በቀረበ ጥናት መነሻነት ቅርብ ጊዜ በርዕሰ መስተዳድር ምክር ቤት ተወስኖ ሸኮ እና ቢፍቱ ከተሞች ከቤንች ሸኮ ዞን፣ ኢሳራ ባሌ እና ዋካ ከተሞች ከዳውሮ ዞን በድምሩ አራት ከተሞች ከፈረጅ አራት ወደ ፈርጅ ሶስት እንዲሸጋገሩ ተደርጓል።
ይህም ለረዥም ጊዜ ሲነሳ የነበረው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከመፍታት ባሻገር ከተሞች ደረጃቸውን በማሳደግ ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ አገልግሎቶች ተደራሽና ቀልጣፋ የሚያደርግ በመሆኑ እነዚህ አራት ከተሞች በ2017 በጀት ዓመት የሰው ኃይል በማሟላት ወደ ስራ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ ።
በክልሉ የብዝሀ ከተሞች እሳቤ መተግበሩ በራሱ በከተሞች አዎንታዊ የፉክክር መንፈስ አድሮ የልማት መነሳሳት እንዲፈጠርና ከዚህ ቀደም ይመሩ ከነበሩት የአመራር ዝንባሌ ባደገ መንገድ እንድናስብ እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል ።
በቅርቡ ታርጫ ከተማ ከፈርጅ ሶስት ወደ ሁለት እንዲሁም ሚዛን አማን እና ቦንጋ ከተሞች ከነበሩበት ከፈርጅ ሁለት ወደ አንድ በማሳደግ በርዕሰ መስተዳድር ምክር ቤት መጽደቃቸውን ያብራሩት አቶ ፀጋዬ ኃይሌ ይህም የክልሉ የከተሜነት ደረጃ ከፍ ለማድረግና የልማት መነቃቃት ለመፍጠር እንዲሁም እንደሀገር በከተሞች እየተተገበረ ላለው ኮሪደር ልማት ያለው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
የከተማ ፕላን ስራ ከፍተኛ የሙያ ስብጥር ያለው ባለሙያ የሚፈልግ እንደሆነም ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ በክልሉ በአንዳንድ ዞኖች የፕላን ዘርፍ ባለሙያዎች ውስንነት እና ለፕላን ትግበራ የሚያግዝ የቴክኖሎጅ ግብዓት እጥረቶች በመኖራቸው በስራ ወቅት ተግዳሮቶችን እያሳደረ እንደሚገኝም አንስተዋል።
በቀጣይ የዘርፉ የባለሙያዎች አቅም ማጎልበት፣ በሚዘጋጁ ፕላኖች ይበልጥ የህዝብ ተሳትፎ የተረጋገጠበት በማድረግ የከተሞች ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በየደረጃው ካለው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቁርጠኝነት መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።
የከተማ ፕላኖችን ከማዘጋጀት ባሻገር ትልቁ ቁልፍ ተግባር መተገበርና ወደ መሬት ማውረድ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የሚዘጋጁ ፕላን የጥራትና ደረጃቸውን ከማረጋገጥ፣ ለስራው አጋዥ መረጃዎች በተገቢው ከመሰብሰብ አኳያ እንዲሁም በፕላን ትግበራ ዙሪያ ያሉ ክፍተቶችን ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መንገድ ማረም ያስፈልጋል ብለዋል አቶ ፀጋዬ ኃይሌ ።
የክልሉ ከተሞች ለኑሮና ለስራ ምቹ ለኢንቨስትመንት ሳቢ እንደሆኑ ለማስቻል በከተማ የሚዘጋጁ ፕላኖች በተግባር ወደ መሬት እንዲወርዱ የአፈጻፀም ሂደታቸውን በየጊዜው በመከታተል በትግበራ ሂደት የሚፈጠሩ ችግሮች ላይ እርምት በመውሰድ ከተሞች ለሰው ልጆች ህይወት ምቹና ቀላል እንዲሆኑ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
የከተማ እስኬጅ ፕላን ማዘጋጀት፣የከተሞች ማዕከላት ለመፍጠር በጥናት መመራት፣የሚዘጋጁ ፕላኖች ትግበራ ውጤታማነት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዲሁም ከተሞች ለኑሮ ምቹና ለኢንቨስትመንት ሳቢ የማድረግ ጉዳይ የኢንስቲትዩቱ ቀጣይ ተልዕኮ እንዲሆኑም ተመላክቷል።
በፍቅር ከበደ
