






የክልሉ ጤና ቢሮ ቀበሌን መሠረት ያደረገ የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ተግባራትን የሚያከናውን ግብረሃይል ወደ ክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ሊያሰማራ ነዉ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያለውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለው ሁሉ አቀፍ ርብርብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ገልጸዋል።
ቢሮው የሚያሰማራው ግብረ ሀይል በየደረጃው ያሉ መዋቅሮችን በማስተባበር በህብረተሰቡ ላይ እየደረሰ ያለውን የወባ በሽታ ስርጭትን መከላከልና መቆጣጠርን መሠረት ያደረገ እንደሆነም ተብራርቷል።
በዘመቻው ዙሪያ ገለፃ የሰጡት የቢሮው ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ቢሮው ከዚህ ቀደም በተከታታይ ከሌሎች የባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በክልሉ ያለውን የወባ በሽታ ስርጭትንና በህብረተሰቡ ላይ እያስከተለ ያለውን ጫና ለመቀነስ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን እንደቆየም አስረድተዋል።
ህብረተሰቡን አሁን ካለው የወባ ስርጭት ጫና ለማውጣት ተግባር ተኮር የሆነና ከተለመደው አሰራር ወጣ ባለ መንገድ ሊሰራ እንደሚገባም አፅንኦት ተሰጥቷል።
በዘመቻው የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት፣ የመከላከያ መንገዶች ተግባራት፣ የመድኃኒት ተደራሽነት ስራዎችና ሌሎች ተያያዥ ተግባራት በጥብቅ ዲሲፕሊንና በኃላፊነት እንደሚከናወንም አቅጣጫ ተቀምጧል።
የወባ ትንኝ ልራባ የሚችሉ ቦታዎችን ማዳፈን፣ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን ማፋሰስ እንዲሁም የአካባቢ ንፅህና መጠበቅ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት ስለሆነ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ለእነዚህ ትግባራት ልዩ ትኩረት ልሰጥ ይገባል።
መላው የጤና ዘርፍ አመራርና ባለሙያዎች የወባ በሽታ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራን ውሎ አዳሩን በማህበረሰቡ ውስጥ በማድረግ ልተገብር ይገባል።
የሚዲያ ተቋማትና ባለሙያዎች ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማህበረሰቡ በማድረስ ማህበረሰቡ ራሱን ከወባ በሽታ እንዲከላከሉ የማድረግ ተግባር ልያከናወኑ ይገባልም ተብሏል።
ቢሮው ወደ ክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ለሚሰማራ ግብረ ሀይል በሁሉም ዘርፍ በቂ ዝግጅት ማደረጉንም ገልጿል።
