የሆርቲካልቸር ምርቶችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳልጥ ዘመናዊ አሰራር ተግባራዊ ተደርጓል

Spread the love

ኢትዮጵያ ለውጪ ገበያ የምታቀርባቸውን የሆርቲካልቸር ምርቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትና ጥራትን ጠብቀው እንዲቀርቡ ዘመናዊ አሰራር ተግባራዊ መደረጉን የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን አስታወቀ።

በምርት ጥራትና ደህንነት ላይ ያተኮረ ብሔራዊ የምርት ጥራት ምዘና ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሒዷል።

ጉባኤው በኢትዮጵያ ተመርተው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የሆርቲካልቸር ምርቶችን የጥራት ደረጃ የሚጠበቅበትንና ተወዳዳሪነታቸው የሚጨምርበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ፤ ኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር ምርቶችን በስፋት የማምረት አቅም ካላቸው ሀገራት መካከል ቀዳሚውን ስፍራ ትይዛለች።

ቀደም ሲል ዘርፉ ካለው የማምረት አቅም አኳያ የነበረው ውጤት እምብዛም እንዳልነበረ አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት የሆርቲካልቸር ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም ዘርፉን እንደ ሀገር ለማሳደግና የሆርቲካልቸር ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግቧል ብለዋል።

ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ለውጪ ገበያ ከምታቀርባቸው የግብርና ምርቶች የጥራት ደረጃ የሚለካው ዘመናዊ ባልሆነ አሰራር እንደነበር አስታውሰው፤ አልፎ አልፎ የጥራት መጓደል ችግሮች ያጋጥሙ ነበር ነው ያሉት።

ለዚህም መንግስት የአሰራር ማሻሻያ በማድረግ ዘመናዊ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረጉን ጠቀመዋል።

በመሆኑም ዛሬ የተካሔደው ጉባኤ ኢትዮጵያ የምርት ጥራትን ለማረጋገጥ እያከናወነች ያለውን ተግባር ለማስተዋወቅና ልምድ ለመለዋወጥ የሚያግዝ እንደሆነም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ በበኩላቸው ጉባኤው የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ብለዋል።

በዋናነት በጉባኤው ላይ በዘርፉ የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገቡ የአውሮፓና የአፍሪካ ሀገራት ተሳታፊ በመሆናቸው ልምድ ለመቅሰምና ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንዳለውም ጠቁመዋል።

በተለይም በሆርቲካልቸር ምርቶች ዙሪያ የአውሮፓ ህብረት ያስቀመጠውን መመሪያና መስፈርት አሟልቶ ለማምረት እንደሚያግዝም አክለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *