በአራት ክልሎች የተካሄደው የ6ኛው ዙር ቀሪና እና የድጋሚ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በተሳካ መልኩ ተጠናቋል፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

Spread the love

በአራት ክልሎች የተካሄደው የ6ኛው ዙር ቀሪና እና የድጋሚ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በተሳካ መልኩ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

የ6ኛው ዙር ቀሪና እና የድጋሚ ምርጫ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

አጠቃላይ የምርጫውን ሂደት በተመለከተም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ መግለጫ ሰጥተዋል።

በ6ኛ ዙር ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በጸጥታና በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫው ሳይካሄድባቸው በቀሩ ክልሎች በዛሬው ዕለት ምርጫው መከናወኑን ተናግረዋል።

የምርጫ ሂደቱን ነጻ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ ለማድረግ ቀደም ብሎ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው፤ የቀሪና ድጋሚ ምርጫው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በአራቱ ክልሎች፣ በ29 የምርጫ ክልሎች እና በ1 ሺህ 218 የምርጫ ጣቢያዎች መካሄዱን ገልጸዋል።

በሁለት ምርጫ ጣቢያዎች ግን የምርጫ ቁሳቁስ ዘግይቶ በመድረሱ ለነገ ተላልፏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በምርጫ ሂደቱ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ድምጽ ሲሰጥ መዋሉን ገልጸው፤ በመተከል ዞን፣ ዳንጉር ምርጫ ጣቢያ ከነበሩ 33 ምርጫ ጣቢዎች መካከል በሁለቱ ምርጫ ጣቢያዎች በቁሳቁስ መዘግየት ሳቢያ ምርጫው ለነገ መተላለፉን ገልጸዋል።

በአንድ ምርጫ ጣቢያ ተመሳሳይ እና ስም ያልተጻፈባቸው መታወቂያዎች ተገኝተው ማጣራት ተደርጎ እርምጃ መወሰዱንም ጠቅሰዋል።

ድምጽ የተሰጠባቸው ሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ ቆጠራ ላይ ሲሆኑ፤ የተወሰኑት ላይ ደግሞ ወደ ምርጫ ክልል ተወስደው እንዲቆጠሩ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ግን በተሳካና ጥሩ በሚባል ሁኔታ መካሄዱን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *