ሚዛኑን የጠበቀ ትብብርና ፉክክር በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ለምን አስፈለገ?

Spread the love

የጋራ ምክር ቤቱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ምቹ መደላድል ፈጥሯል::”

የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ ባሻ

የምርጫ ህጉ አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ካስቀመጣቸው ኃላፊነት ያለባቸው የምርጫ የባለድርሻ አካላት ዝርዝር አንዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ነው፡፡ ይህ ምክር ቤት የሚመሠረተው በምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ህጉ የተቀመጡ ድንጋጌዎችንና ሌሎች የጋራ ጉዳዮችን ተግባራዊ ለማድረግና በምርጫው ሂደት በሚነሱ ልዩ ልዩ የአፈፃፀም፣ የዴሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብት ጉዳዮችንና የህግ የበላይነትን በኢትዮጵያ ለማጎልበት በሚያግዙ ጉዳዮች ላይ በመመካከር ችግሮችን እያቃለሉ ለመጓዝ ይችሉ ዘንድ ነው፡፡

ይህንንም ተፈፃሚ ለማድረግ መጋቢት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. 116 የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱን የአሠራር ደንብ ለመወሰን የቃል ኪዳን ሰነድ ፈርመዋል፡፡ ይህ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአሠራር ደንብ የቃል ኪዳን ሰነድ በፈረሙት እና ወደፊት በሚፈርሙት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን ነው፡፡

በ2015 ዓ/ም በይፋ የተመሠረተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ባለፉ ሁለት ዓመታት በልማት፣ በሠላምና በዴሞክራሲ ስረዓት ግንባታ እንዲሁም በአጠቃላይ ክልላዊና ሀገራዊ ጉዳዮች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ነው የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ ባሻ የሚናገሩት።

የክልሉ መንግሥት ከምክር ቤቱ ምሥረታው ጀምሮ መዋቅሩን በፋይናንስና ሎጀስቲክ በመደገፍ በክልሉ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምቹ የፖለቲካ ምህዳር ፈጥሮ የፖለቲካ ፕሮግራምና ፖሊሲዎቻቸውን በነጻነት ለአባልና ደጋፊዎቻቸው እንዲያደርሱ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑም ነው የተገለጸው።

አምስት የስራ አስፈጻሚ አባላት ያቀፈው የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በክልሉ በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የካፋ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት፣ የካፋ አረንጓዴ ፓርቲ እና የሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እንዲሁም ገዢው የብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ 8 ገደማ የሚሆኑ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በጥምረት ያቀፈ ሲሆን አጠቀላይ ተግባራትን በጋራ ምክር ቤቱ በፀደቀው የቃልኪዳን ሰነድ መሠረት ተቋማዊ ዕቅድ በመንደፍ እያከናወነ እንደሚገኝ ነው የተነገረው።

ጽ/ቤቱን በክልሉ የአስተዳደርና የፖለቲካ መቀመጫ ከተማ ቦንጋ ያደረገው የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚዎች በወር አንድ ጊዜ፣ የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ ደግሞ በሶስት ወር አንድ ጊዜ (ሩብ ዓመት) በመሰብሰብ አጠቃላይ ተግባራትን በመገምገም በቀጣይ የትኩረት መስኮች ላይ ወጥ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጡ ነው አቶ ግርማ ያብራሩት።

አደረጃጀቱን በየደረጃው ባለው የአስተዳደር መዋቅር በማዋቀር የምክር ቤቱን አውንታዊ ሚና ለማጎልበት በተሰጠው ትኩረት ሁለትና ከዚያ በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚንቀሳቀሱባቸው ሁሉም የክልሉ አከባቢዎች የጋራ ምክር ቤት መቋቋሙን የጠቆሙት አቶ ግርማ ባሻ  የካፋ እና የሸካ አካባቢዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በብዛት የሚንቀሳቀሱባቸው አከባቢዎች ሲሆኑ በአመዛኙ ምዕራብ ኦሞ እና ኮንታ ዞን አካባቢዎች በቁጥር አነስተኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚንቀሳቀሱባቸው ነው የገለጹት።

ከምክር ቤቱ ምሥረታ ወዲህ በተሰሩ ተግባራት ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ግርማ ተቋማዊ ዕቅድ በማዘጋጀትና ሀብት በማፈላለግ የተቋሙን ተልዕኮ ለማሳካት መጠነ ሰፊ ተግባራት መከናወኑንና በዚህም የጋራ ምክር ቤቱ አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር ግንባታ፣ በሠላምና መልካም አስተዳደር እንዲሁም በዲሞክራሲ ስረዓት ግንባታ ላይ አውንታዊ ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ከመንግሥት ጋር በመተባበር በክልሉ በሚሰሩ ሁለንተናዊ የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት ላይ በቂ ግንዛቤ የመፈጠርና አሳታፊነትን የማረጋገጥ ተግባር ተከናውኗል ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሀገር ግንባታ ላይ ያላቸውን ሚና በውል ተረድተው በአግባቡ እንዲወጡ ከማስቻል አኳያ የአቅም ግንባታ ስልጠና ከቦንጋ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር መሰጠቱን ያወሱት የምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ በዚህም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፖለቲካ ፕሮግራምና ፖሊሲዎቻቸው በተጓዳኝ ሚዛን የጠበቀ ፉክክርና ትብብር በማጠናከር ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ ምቹ መደላድል መፈጠር መቻሉን ተናግረዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚገጥማቸውን ማነቆዎች በመለየት በየደረጃው ካለው የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ አመራሮች ጋር በመሆን እየፈታ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ግርማ ለአብነት በዳውሮ ዞን ከኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት እንዲሁም በሸካ ዞን ማሻ ወረዳ ከሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የቀረቡ ቅሬታዎችን ተቀብለው በመፍታት የፖለቲካ ስራዎቻቸውን በነጻነት እንዲያከናውኑ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ለምክር ቤቱ በፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀርቡ የፖለቲካ ስራዎችን በነጻነት ከመከወን አንጻር በተላይም የቢሮው ክራይ፣ የመሰብሰቢያ አደራሽ ማግኘትን የመሳሰሉ ተመሳሳይ ቅሬታዎች ትርጉም ባለው መልኩ እየተፈቱ እንደሆነና በሂደቱም ለዚሁ ተግባር እንቅፋት የሚሆኑ አካላትን የማስጠየቅ ስራዎች መኖራቸውንም ነው ሃላፊ የገለጹት።

በተመሳሳዩ ባልተገባ መልኩ ጫና የሚደርስባቸው የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራር የመንግሥት ሠራተኞች ቅሬታን ተቀብሎ የእርምት ማስተካከያ መደረጉን የሚገልጹት ሃላፊው ይሁን እንጂ የፓርቲ አባላትን እንደ ሽፋን በመጠቀም ያልተገባ ጥቅም ለማገኘት መሻት፣ የከፋ ችግር ያለ አስመስሎ ያልተጣሩ ጉዳዮችን በሚዲያ (ማህበራዊ ሚዲያ) ማስተጋባት እና ከተጠያቂነት ለመሸሽ የሚደረጉ ጥረቶች መኖራቸውን አልሸሸጉም።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በተናጠል በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ይስተዋል የነበረው የጠላትነት ፍረጃ ተወግዷል የሚሉት አቶ ግርማ አሁን ላይ በተጨባጭ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በየአካባቢው ግንባር ቀደም የልማት ተሰላፊ እንዲሁም የሠላም አምባሳደርነት ሚናውን እየተወጡ መሆኑን ይገልፃሉ። ለዚሁም እንደማሳያ በካፋ ዞን የቦንጋ ከተማ መልሶ ማልማት እንቅስቃሴ እና በዳውሮ ዞን የባህል ማዕከል ግንባታ ላይ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከህዝብ ጎን በመቆም የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑ ተመላክቷል።

በየአካባቢው ከመንግሥት ጋር ተግባብተው የመስራት ባህል እየዳበረ መምጣቱ ሁሉም ፖርቲዎች ለሚታገሉት ህዝቦች ሁለንተናዊ ጥቅም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ግርማ ፓርቲዎቹ በክልሉ የተገኘው ሠላም እንዲፀና አባላትና ደጋፊዎቻቸውን በማስተባበር እያደረጉት ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

ምክር ቤቱ እንደ አንድ የማሀበራዊ መሠረት በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መድረኮች ላይ ላይ በንቃት በመሳተፍ ለዘላቂ ሠላም ያለውን ጽኑ አቋም እያንፀባረቀ እንደሚገኝ የሚገልጹት አቶ ግርማ ከዚህም ባሻገር መንግሥት የዜጎችን ማህበራዊ ዋስትና ለማረጋገጥ በሚያደርጓቸው የክረምት በጎ ተግባር ላይ በመሳተፍ በኮንታ ዞን ለአንዲት አቅመ ደካማ እናት ቤት ገንብተው መስጠት መቻሉን ተናግረዋል።

እንደአጠቃላይ ምክር ቤቱ በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምቹ የፖለቲካ ምህዳር በመፈጠርና በሂደቱ የሚገጥሙ ችግሮችን ፈጥኖ በማረም ለዲሞክራሲ ስረዓት ግንባታ አውንታዊ ሚናውን መወጣት የተቋሙ ተልዕኮ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ግርማ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግሥት ጋር በጋራ ጉዳዮች በትብብር መንፈስ በመስራት ለህዝብ ጥቅም እንዲሰሩ ለማስቻል የሚረዱ ትርጉም ያላቸው መደረጋቸውን አብራርተዋል።

በስተመጨረሻም በምክር ቤቱ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማጎልበት እና ጉድለቶችን በልካቸው በማረም የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ በየደረጃው የማጠናከር ስራ እንደሚቀጥል የገለጹት አቶ ግርማ ከክልሉ መንግሥት ጋር በጋራ ጉዳዮች በትብብር የመስራት ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *